ኢትዮጵያ በስንዴና ሌሎችም የግብርና መስኮች እያሳየች ያለችው ውጤት ለአፍሪካ ቀንድ ተስፋ ሰጪና ምሳሌ የሚሆን ነው- የፋኦ አስተባባሪ

168

ጥቅምት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በስንዴና ሌሎችም የግብርና መስኮች እያሳየች ያለችው ውጤት ለአፍሪካ ቀንድ ተስፋ ሰጪና ምሳሌ መሆኑን በጂቡቲ የፋኦ አስተባባሪ ዶክተር ፋሎው ጉዬ ተናገሩ።

የአፍሪካ ቀንድ በአየር ንብረት ለውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠቁት አካባቢዎች አንዱ ሲሆን፤ በቀጣናው ድርቅ፣ ጎርፍና የበረሃ አንበጣ የምግብ ዋስትና ፈተና ሆነዋል።

ከዚህም ባለፈ የቀጣናው ማህብረሰብ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ግጭቶች፣  በውስጣዊ ፖለቲካዊ ቀውሶች፣ በግብርና ምርቶች ዋጋ መጨመር ሳቢያ  የተለያዩ ችግሮች ተጋርጠውበታል።

በዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የጂቡቲ አስተባባሪ ዶክተር ፋሎው ጉዬ፤ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር ያለበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ችግሩን በቅጡ የተገነዘቡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የቀጣናው ሀገራት መንግስታት  የምግብ ዋሰትናን ለማረጋገጥ በቆራጥ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ መሆናቸውን አንስተዋል።

በተለይም የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ፈተናዎችን ተቋቁሞ በቂ ምርት የሚያስገኝ የሰብልና የእስሳት ምርታማነት ጉዞ መጀመራቸውን በማንሳት።

በዚህ ረገድ የቀጣናውና የአፍሪካ ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ በስንዴና ሌሎች የግብርና መስኮች የጀመረችው እመርታዊ ጉዞ ለቀጣናው ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በስንዴ እያሳየች ያለችውን ስኬት ሌሎች የቀጣናው ሀገራትም ማሽላ፣ ገብስ፣ በቆሎና ሌሎች የጥራጥሬ ሰብሎችን ላይ በማተኮር በቂ ምርት በማምረት ከጥገኝነት መላለቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በግብርና ቴክኖሎጂ፣ በሰፊ የሰው ኃይልና መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ሰፊ የኢንቨስትመንት ትኩረት ስኬታማ ስራዎችን እያከናወነች ነው ብለዋል።

በተለይም የግብርና ሜካናይዜሽን ላይ በተቋም ደረጃ አርሶ አደሮችን በመደገፍ በኩል የጀመረችው ለውጥ ለቀጣናው ሀገራት ትልቅ ትምህርት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ሌሎች ሀገራትም ከዚህ ተሞክሮ ወስደው የግብርናውን ዘርፍ መለወጥና የቀጣናውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚገባቸው መክረዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰፊ የእንስሳትና የዓሳ ሃብት እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ለዚህ ዘርፍም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ነው ዶክተር ፋሎው የጠቆሙት።

በተለይም ጤናማ የእንስሳት ሃብት ልማትን በመተግበር ወደ መካከለኛው ምስራቅና ሌሎች ሀገራት የሚደረገውን የእንስሳት ሽያጭ በማጠናከር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም