የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የተቋማትና አጠቃላይ የዜጎች ጥረት ሊታከልበት ይገባል - የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር

125

ጥቅምት 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የተቋማትና አጠቃላይ የዜጎች ጥረት ሊታከልበት የሚገባ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለጸ፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር 3ኛው አገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ምክንያት በማድረግ "የተቀናጀ የሳይበር ደህንነት ለአገር ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ ከተለያዩ ባድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ጉታ በመድረኩ ላይ የተናገሩት፤ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ የተቋማትና አጠቃላይ የዜጎች ጥረት ሊታከልበት ይገባል።

የአቅም ውስንነትና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ችግር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የትምህርት ተቋማት ወጣቶችን ማስተማርና ማሰልጠን አለባቸው ነው ያሉት።

በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ከሚደረገው መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት ባለፈ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ህጻናት እና ወጣቶች በልዩ ስልጠና መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት በትምህርት ቤቶች ከታች ጀምሮ የማሰልጠን ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ፤ በተለያዩ ተቋማት ላይ የሚፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ተናግረዋል።

የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ሂደት ዩኒቨርሲቲዎች የጎላ ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ከሆኑ ተቋማት መካከል የፋይናስ ዘርፉ ተጠቃሽ መሆኑን የተናገሩት የአዋሽ ባንክ የስትራቴጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ ሰለሞን ጀቤሳ፤ የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም