የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሊሻሻል ይችላል ተባለ

192
አዲስ አበባ መስከረም 14/2011 በኢትዮጵያዊያን መካከል ብሄራዊ መግባባት የሚፈጥር ሌላ ሰንደቅ ዓላማ እንዲቀረፅ ሀሳብ የሚቀርብ ከሆነ ሊሻሻል እንደሚችል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ። ይህ እስኪሆን ግን በህገ-መንግስቱ የፀደቀውንና በሥራ ላይ የሚገኘውን የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ የማክበርና የማስከበር ግዴታ መኖሩን መረዳት እንደሚያስፈልግም አስገንዝቧል። የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት በ1987 ዓ.ም ሲፀድቅ የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ እኩል አግድም የተሰመሩ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት እንዲሁም መሀሉ ላይ አርማ ያለው እንዲሆን ተደንግጓል። የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ይወክላል የተባለው አርማና ትርጉሙ በአዋጅ ቁጥር 654/2001 የይዘትና አጠቃቀም ዝርዝር መረጃዎች አካቶ ስራ ላይ እንዲውልም ተደርጓል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህ ከ24 ዓመት ጀምሮ በሥራ ላይ ያለው ሰንደቅ አላማ የግጭትና የፀብ መነሻ ሲሆን ይስተዋላል። ምክር ቤቱ "ሰንደቅ ዓላማችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን" በሚል መሪ ሐሳብ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክት አድርጎ በመጠቀም ረጅም ታሪክ ያላት አገር እንደሆነች ተናግረዋል። ሰንደቅ ዓላማን በተመለከተ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ካሁን ቀደም የተደረጉ እንቅስቃሴዎች አጥጋቢ ባለመሆናቸው ለግጭት የዳረጉ ልዩነቶች ተፈጥረዋል ብለዋል በንግግራቸው። በሥራ ላይ ካለው የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ በዜጎች መካከል የጋራ መግባባት እንደሌለ ምልክቶች እየታዩ ነውም ብለዋል። ወይዘሮ ሽታዬ እንደሚሉት ህዝቡ አሁን ያለውን ሰንደቅ አላማ በግድ እንዲቀበል ሲደረግ የነበረው አካሄድ መቆም አለበት። በመሆኑም ከአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ ያለውን ልዩነት የፀብና የግጭት መንስኤ ከማድረግ ይልቅ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የተሻለ ሃሳብ ማፍለቂያ ማድረጉ ይበጃል ብለዋል። ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በሚከበረው የሰንደቅ አላማ ቀን የልዩነቶቹን መነሻ ለማወቅ ከወጣቶችና በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር የውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ "ብሄራዊ መግባባት የተፈጠረበትና አንድ ወጥ መገለጫ ሰንደቅ ዓላማ ሊኖራት ይገባል" ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔዋ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን ለማጥበብ በሰለጠነ አካሄድ መወያየት ይገባል ነው ያሉት። ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አቀፍ መድረኮች የሉዓላዊነት መገለጫ ምልክት በመሆኑ ኅብረተሰቡ ይሆነኛል የሚለውን የተሻለ ሰንደቅ ዓላማ ካቀረበ ለማሻሻል ዝግጁነት እንዳለም ወይዘሮ ሽታዬ አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡ ያመነበትና ይሆነኛል ያለውን ከመረጠ ሰንደቅ ዓላማው ህገ-መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት የማይሻሻልበት ምክንያት እንደሌለም አክለዋል። በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና አስተማማኝ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማምጣት የጋራ መግባባት የተደረሰበትና ዜጎችን የሚወክል ሰንደቅ አላማ እንደሚያስፈልግም ወይዘሮ ሽታዬ ጠቁመዋል። ይህ ሲደረግ ግን አሁን ያለውና በህገ-መንግስቱ የፀደቀውን ህጋዊ ሰንደቅ አላማ የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም