አየር መንገዱ በዓመት ከአውሮፕላን ጥገና ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ አግኝቻለሁ አለ

117
አዲሰ አበባ መስከረም 14/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአውሮፕላን ጥገና በዓመት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት አየር መንገዱ ባለው የጥገና ማእከል ከራሱ አውሮፕላኖች አልፎ ለሌሎች አገራት አውሮፕላኖች የጥገና አገልግሎት ይሰጣል። የአንጎላ፣ ሩዋንዳ፣ ሞዛምቢክ፣ ካሜሮን፣ ናይጄሪያ፣ ቶጎ፣ ቻድና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ አውሮፕላኖች ጥገናው ከሚደረግላቸው መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑም አብራርተዋል። በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሰጠው የአውሮፕላን ጥገና ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘቱን ነው አቶ ተወልደ የገለጹት። ጥገናው ከአገሪቱ አልፎ ለሌሎች አገራት መሰጠቱ አየር መንገዱ ያለውን ተፈላጊነትና የአገልግሎት ጥራት ከፍ ያደርገዋልም ነው ያሉት። በተጨማሪም ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ የጥገና አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች የስራ እድል ፈጠራና የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በዚያው ልክ እየጨመረ መምጣቱንም አብራርተዋል። ይህም ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአገልግሎት አሰጣጡ ባሻገር በተለያዩ ዘርፎችም ተመራጭ እንዲሆን አስችሎታል ይላሉ። ሌላው ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መሰረት በማድረግ የጥገና አገልገሎት መሰጠቱም አየር መንገዱ ያለበትን አቅም እንዲያጎለብት ከማድረግ አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱ እንዲጨምር አሰተዋጽኦ አበርክቶለታል ብለዋል ስራ አስፈጻሚው።     የኢትዮጵያ አየር መንገድ 108 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን በዚህም በአፍሪካ የመጀመሪያውን ደረጃ ሲይዝ በዓለም የ24ኛ ደረጃ ስፍራን መያዙን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም