ዜጎች ስለ ሰላምና አንድነት የሚናገሩትን በተግባር ሊኖሩት ይገባል

46
አዲስ አበባ መስከረም 14/2011 ዜጎች ስለ ሰላምና አንድነት የሚናገሩትን በተግባር ሊኖሩት ይገባል ስትል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ጥሪ አቀረበች። የኃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት አካላት፣ ወላጆችና መምህራን ወጣቱን ስለ ሰላምና አንድነት በማስተማር በስነ-ምግባር የታነጸ ዜጋ የማፍራት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብላለች። የቤተ-ክርስቲያኗ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የ2011 የደመራና የመስቀል በዓልን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠመ ያለው ሁከትና ብጥብጥ የሰው ህይወት በቀላሉ እንዲጠፋና ንብረትም እንዲወድም እያደረገ ነው። ይህ ደግሞ ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣን የሰላምና የአብሮነት ታሪክ የሚያጠለሽና አገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስድ ነው ብለዋል። ''የጥንት አባቶች ያወረሱን ሰላምን፣ አብሮ መብላትን፣ አብሮ መጠጣትን ፣መደጋገፍን መተዛዘንን፣ ኢትዮጵያዊ ወኔን፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ነው'' ያሉት ኃላፊው መከፋፈልና ጥላቻን በመተው ኢትዮጵያዊነትን በተግባር ማንፀባረቅ እንደሚገባ አመልክተዋል። ሁሉም አስተያየት ሰጪ ስለ አገር ሰላምና አንድነት በቃሉ የሚናገረውን በተግባር ማሳየት እንዳለበት በመጠቆም። ''በቀላሉ የተጀመረ ነገር ነገ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል'' ያሉት አቡነ ዲዮስቆሮስ እንዲህ አይነቱ ነገር እየሰፋ ሄዶ አገሪቱን ከጥቅም ውጪ እንዳያደርጋት ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል። የቤተክርስቲያኗ የኃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት አካላት፣ ወላጆችና መምህራን ወጣቱን ስለ ሰላምና አንድነት በማስተማር በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ የማፍራት ግዴታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም