የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከአየር ክልል ዘብነቱ ባሻገር በግብርና ልማት ለህዝብ የሚተርፉ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል

164

ጥቅምት 13/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከአየር ክልል ዘብነቱ ባሻገር በግብርና ልማትም ራሱን ከመቻል አልፎ ለማህበረሰቡ ለመትረፍ በትጋት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

አየር ሃይሉ በተያዘው የምርት ዘመን የጀመረው የስንዴ ልማት አበረታች ደረጃ ላይ ስለመሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር “ማጽዳት፣ ማስዋብና ማልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ካከናወናቸው የግብርና ስራዎች መካከል በተቋሙ ግቢ ስንዴን ማልማት አንዱ ነበር።

ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ፣ ከምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ከአካባቢው አርሶ አደሮችና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ከሶስት ወራት በፊት የዘራው የስንዴ ሰብል ለፍሬ በቅቶ ተጎብኝቷል።

በአየር ሃይሉ የፋይናንስ ስራ አመራር ዳይሬክተር ኮሎኔል በሻህ ደገፋ፤በተያዘው የምርት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ28 ሄክታር ያላነሰ መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን ገልጸዋል።

አየር ሃይል የኢትዮጵያን የአየር ክልል በመቆጣጠር ለአገር ሉአላዊነት መከበር የላቀ ድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው በግብርና ልማትም የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በተቋሙ ሰፊ ግቢ ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ሰብሎችን በማልማት የላቀ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ኮሎኔል በሻህ ገልጸዋል።

ዘንድሮ ካለማው ሰብል ከስንዴ ብቻ 2 ሺህ 500 ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን ጠቁመዋል።

በዶሮ፣ በከብት፣ በንብና ሌሎች የልማት መስኮችም ለመሰማራት ዝግጅት ማድረጉን በመጠቆም።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በአካባቢው ስንዴና አቡካዶን ጨምሮ በጋ ከክረምት ሰብል እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

May be an image of 1 person, grass and sky

በዞኑ ያለውን ዕምቅ አቅም ለመጠቅም ከአርሶ አደሮች ማሳ ባለፈ የግልና የመንግስት ተቋማት በራሳቸው ግቢ ውስጥ ሰብል እንዲያለሙ በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዘንድሮ በጀመረው የስንዴ፣ የጤፍ እና ሌሎች የጓሮ አትክልት ልማት ላይ የባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል በመደረጉ በሰብል ልማቱ ውጤታማ እየሆነ መሆኑን ገልጸዋል።

ኬምቴክስ የተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም የፀረ አረምና የፀረ ዋግ መድሃኒት በነፃ በማቅረብ የድርሻውን የተወጣ መሆኑን ነው የተናገሩት።

አየር ሃይሉ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ጥልቅ ትስስር የፈጠረና የማህበረሰቡን የባለቤትነት ስሜት ያሳደገ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለሌሎች ትልቅ ተሞክሮ እንደሚሆን አውስተዋል።

በቀጣይም ከመኸር በተጨማሪ በበጋ ወቅት ማምረት እንዲችል ዞኑ በትብብር ይሰራል ነው ያሉት።

May be an image of 1 person and outdoors

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አንጋፋው ተመራማሪ ዶክተር ካሳሁን ዘውዴ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል የጀመረችውን አሁናዊ ንቅናቄዎች አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ የግብርና ጸጋዎችን በቁርጠኝነት መጠቀም ከቻለች ከራሷ አልፋ ሌሎች እንደምትተርፍ ተናግረዋል።

ዶክተር ካሳሁን የኢትዮጵያ አየር ሃይል የጀመረው ስራ ለሌሎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ አክለዋል።

May be an image of 7 people, military uniform and outdoors

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፤ከጉብኝዎቹ ጋር ባደረጉት ውይይት አየር ሃይሉ የሰው ሃይል፣ ትጥቅ ማሟላትና የውጊያ መሰረተ ልማት መገንባት ከሚሉት የትኩረት አቅጣጫዎች ባሻገር የተቋሙን ሰፊና ለም መሬት በማልማት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ከሰብል ልማት ባለፈ በእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ራሱን ለመቻል አቅዶ እየሰራ ሲሆን ተቋሙ በግብርና ምርቶች ከራሱ አልፎ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለመትረፍ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም