ትኩረት የሚሹ ሃሩራዊ በሽታዎችን ለማከምና በዘላቂነት ለማጥፋት እየተሰራ ነው

92
አዲስ አበባ መስከረም 14/2011 ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች ተብለው የተለዩ ከ20 በላይ በሽታዎችን ለማከምና በዘላቂነትም ለማጥፋት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ። አለም ዓቀፍ ትኩረት የሚሹ የሃሩራማ በሽታዎች ጉባኤ ''የመጨረሻዎቹን አንድ ቢሊዮን ለመድረስ እንረባረብ'' በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች ከድህነትና ከግል ንፅህና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚከሰት የበሽታ አይነት ሲሆን አሁን ላይ ከ149 በላይ በሆኑ አገሮች እንደሚታይ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። በሽታው ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ትስስር ሊቀመንበር ታንያ ዉድ እንደሚሉት፤ በሽታው በቀላሉ በህክምና የሚድን ቢሆንም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባላቸው አገሮች በስፋት ይታያል። በትስስር በሽታው ላይ የሚሰሩ ተቋማት አሁን ላይ ከ100 አገሮች በላይ ተሳትፎ በማድረግ በሽታውን በመቀነስ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ሊቀመንበሯ አክለውም በጋራ ትብብር ተጠናክሮ መስራት ከተቻለ በሽታውን በጥቂት ጊዜ ማጥፋት እንደሚቻል ተናግረዋል። ከተለዩ 20 ሃሩራማ በሽታዎች በኢትዮጵያ ዘጠኝ በሽታዎች የሚገኙ ሲሆን ኢትዮጵያ በሽታውን ለማጥፋት በትኩረት እንደምትሰራ ነው ትስስሩ ያስታወቀው። በኢትዮጵያ ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች መካከል ትራኮማ፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትል፣ ስጋ ደዌ፣ ቢሊሃርዚያ፣ ዝሆኔ፣ ፎከትና ካላዛር ይገኙበታል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች ቡድን መሪ አቶ ነብዩ ንጉሱ ሃሩራማ በሽታዎችን አይነቶች ለመለየት በ859 ወረዳዎች የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል። በሽታዎቹን ለመከላከል በ2020 የህብረተሰብ ስጋት መሆናቸውን ለማስቀረት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዕቅድ አዘጋጅቶ እንደሆነ ተናግረዋል። የበሽታዎቹን ስርጭት መቶ በመቶ ለመግታት እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ነብዩ የትራኮማ የአይን ቀዶ ጥገና ለመስጠት በተደረገው ጥረት ቀጠሮ ከሚጠባበቁ ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑት ህክምና እንዳገኙ ገልጸዋል። በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ አፋርና ደቡብ ክልሎች ውስጥ የሚገኘውን የካላዛር በሽታ በማጥናት በአምስት መንገዶች ህክምና መስጠት መቻሉን ገልጸዋል። በትራኮማ የመያዝ እድል ዝቅ በማድረግም በ89 ወረዳዎች የሚገኙ ተጠቂዎች ከአመታዊ የመድሃኒት ስርጭት ማስወጣት ተችላል ሲሉ ገልፀዋል። በቀጣይም የማህበረሰብ የመድሃኒት እደላ፣ ህክምናና የአካባቢ የግል ንፅህና አጠባበቅ ላይ ለመስራት አራት ስትራቴጂዎች ተቀርፀው የ2020 ግብን ለማሳካት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም