መንግስት ለአካል ጉዳተኞች የሰጠው ትኩረት ብሩህ ተስፋ እንደፈጠረለት ፌዴሬሽኑ ገለጸ

104
አዲስ አበባ  መስከረም 14/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደኃላፊነት ከመጡ ወዲህ መንግስት ለአካል ጉዳተኞች የሰጠው ትኩረት ብሩህ ተስፋ እንደፈጠረለት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ። የፌዴሬሽኑ ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በኢትዮጵያ በፍቅር፣ አንድነት፣ ሰላምና ሌሎች ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች እየታዩ ነው። ''አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍም እንዲሁ የጀመሯቸው እንቅስቃሴዎች ነገን የተሻለ ለማድረግ ተስፋ እያሳየን ነው'' ብለዋል። ቀደም ሲል በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ላይ ህጎችና ደንቦች ሲወጡ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ህግ ከመውጣቱ በፊት ፌዴሬሽኑ ተሳትፎ እንዲያደርግ መጠየቁ መንግስት ማድረግ ያለበትን እየተወጣ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ የአካል ጉዳተኞች ጥረትም ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል። "ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰሩ የሲቪክ ማህበራትን ለማወያየት ቀጠሮ መያዛቸውንም ሰምተናል ይህም ለኛ ሌላው ተስፋ የሰጠን ጉዳይ ነው" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአሜሪካ ከኢትዮጵያውያን ጋር ከነበሯቸው መድረኮች በአንዱ የዳያስፖራው ድጋፍ አካል ጉዳተኞችን የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል። በዚህም ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ሰጪ ምላሽ ያገኙ ሲሆን ድጋፉ ለአካል ጉዳተኞች መርጃ መሳሪያና ለሌሎች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ እንደሚውል መግለጻቸውም ለፌዴሬሽኑ ተስፋ የሰጠ ቃል እንደሆነ ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ በማህበራት አደረጃጀት፣ በአካቶ ትምህርት እንዲሁም ሌሎች የልማት ስራዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ተደርገው እንደሚፈጸሙ እምነት ማሳደራቸውን ገልጸዋል። "ጠቅላይ ሚኒስትሩ የከፈቱትን በር እንደ ትልቅ አጋጣሚና አብዮት ነው የምናየው" በማለት የተናገሩት አቶ አባይነህ እድሉን በመጠቀም የኢትዮጵያ አካል ጉዳኞች ህብረተሰቡንም ሆነ መንግስትን የሚጠቅሙና የሚያግዙ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ቶፊቅ ሃምዲኑር ''አካል ጉዳተኛ ሲባል ከውጭ የሚታየው ላይ ትኩረት ስለሚደረግ መስማት የተሳናቸው ይረሳሉ'' ብለዋል። አካል ጉዳተኞች ጉዳታቸውና ፍላጎታቸው እንዲሁም ችግራቸው ተለይቶ እንደሚሰራ እምነታቸውን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ያህል አካል ጉዳተኞች አሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም