የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

75
ጎባ መስከረም 14/2011 በአርሶ አደሩ ዘንድ የሚታየውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር ለማቃለል እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ ምርጥ ዘር በወቅቱና በሚፈልጉት መጠን ማግኘታቸው ምርታማነታቸውን እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን  አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አርሶ አደሮች ገልፀዋል፡፡ በኢንተርፕራይዙ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ መሀመድ አብዱልወሃብ እንደተናገሩት ኢንተርፕራይዙ በዋናነት የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ካመረተው ምርጥ ዘር ለዘንድሮው የመኽር አዝመራ አገልግሎት እንዲውል 95 ሺህ 271 ኩንታል ምርጥ ዘር አሰራጭቷል፡፡ "ስርጭቱ እንደየወረዳዎቹ የስነምህዳር ሁኔታ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ በሚዘልቀው የዘር ወቅት ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል ። ለአርሶ አደሩ እየተሰራጩ ከሚገኙት ምርጥ ዝርያዎች መካከል የዋግ በሽታን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡና ከተለያዩ የግብርና ምርምር ማዕከላት በምርምር ተገኝተው በኢንተርፕራይዙ የተባዙ የስንዴ፣ ገብስና የባቄላ ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ አቶ መሀመድ እንዳሉት ኢንተርፕራይዙ ከምርምር ተቋማት በምርምር የወጡ መስራች ዝርያዎችን ተቀብሎ በራሱ እርሻ ላይ ካባዛ በኋላ አዋጭነታቸውን በመገምገም ከሙያዊ ምክር ጋር ለአርሶ አደሩ ያሰራጫል፡፡ በኢንተርፕራይዙ የሚባዙ ምርጥ ዘሮችን የሚጠቀሙ የአካባቢው አርሶ አደሮች ምርታማነታቸው ከማደጉም በላይ ለምርጥ ዘር ያላቸው ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመራ መምጣቱን ጠቁሟል፡፡ በሲናና ወረዳ ሰልቃ ቀበሌ የኢንተርፕራይዙን ምርጥ ዘር ከሚጠቀሙ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ማህሙድ አህመድ ምርጥ ዘር በወቅቱና በሚፈልጉት መጠን ማግኘታቸው ምርታማነታቸው እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያደረገላቸው መሆኑን  ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት የአካባቢውን ዝርያ በመጠቀም ከአንድ ሄክታር መሬት ያገኙት የነበረው የስንዴ ምርት ከ20 ኩንታል እንደማይበልጥ የጠቀሱት አርሶ አደር ማህሙድ ከኢንተርፕራይዙ ያሚያገኙትን ምርጥ ዘር መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ በሄክታር እስከ 65 ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻላቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ ከኢንተርፕራይዙ የሚቀርብላቸውን ምርጥ ዘር መጠቀም ከጀመሩ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ በወረዳው የሻሎ ቀበሌ አርሶ አደር ዩሱፍ አብደላ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት 3 ሄክታር ማሳቸውን ምርጥ ዘርና ሙሉ የግብርና ፓኬጅ በመጠቀም እያለሙ መሆናቸውንና ከአምና የተሻላ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደር በከር ሀሰን በበኩላቸው የአካባቢ ዘር ይጠቀሙ በነበረበት ወቅት የሚያገኙት ምርት አነስተኛ በመሆኑ የቤተሰባቸውን የምግብ ፍጆታ ለማሟላት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል ፡፡ በምርጥ ዘር ምርታማነታቸው በመጨመሩ በአሁኑ ወቅት የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ከአካባቢ አርሶ አደሮች ጋር ተቀናጅተው በክላስተር በማልማት ለገበያ ለማቅረብ ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በዞኑ የሚገኙ ሮቤና ሲናና እርሻዎችን ጨምሮ በምስራቅ አርሲ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሄራሮ፣ ሁንጤና ቢሊቶ ስራሮ የሚባሉ 15 ሺህ 846 ሄክታር የሚለማ መሬት ያስተዳድራል። ከዚህ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ የእርሻ ማሳዎች ለምርጥ ዘር ብዜት እንደሚውሉ ከኢንተርፕራይዙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡ በባሌ ዞን ከሐምሌ ወር አጋማሽ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ያለው ጊዜ የመኸር እርሻ የዘር ወቅት መሆኑን ይታወቃል  ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም