የቡና ግብይት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ

82
ጎባ መስከረም 14/2011 የቡና ምርትን በብዛትና በጥራት ለገበያ ለማቅረብ ባለው  ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ። " የቡናና ቅመማ ቅመም ምርት ጥራትን በመጠበቅ አስተማማኝ ገበያና ዋጋን እናረጋግጠለን!"በሚል መሪ ሀሳብ  በባሌ ሮቤ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄዷል፡፡ የውይይቱ  ተሳታፊ ቡና ነጋዴዎችና አቅራቢዎች እንዳሉት የህገወጥ ንግድ መበራከት፤ በምርት ገበያ በኩል የሚደረጉ ግብይቶች ላይ ኢ-ፍትሃዊ የንግድ አሰራር መኖር ምርቱን በሚፈለገው መጠንና ጥራት ለገበያ እንዳያቀርቡ ማነቆ ሆኖባቸዋል ። በዞኑ በርበሬ ወረዳ በቡና ንግድ የተሰማሩ አቶ ለሜቻ ሹካራ በአካባቢያቸው እየተበረከተ የመጣው ህገወጥ የቡና ግብይት ህጋዊውን ነጋዴ ከጨዋታ ውጪ እያደረገው መምጣቱን ተናግረዋል። ብዙ ወጪ ተደርጎባቸው ለማዕከላዊ ገበያ ከሚቀርበው ቡና አመርቂ ውጤት ስለማይገኝ በየደረጃው ያለው ባለሀብትም ከአርሶ አደሩ ላይ በአነስተኛ ዋጋ ለመግዛት  ይገደዳል፡፡ አቶ ለሜቻ  በቡና ንግድ ግብይት ሰንሰለት ውስጥ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ "በምርት ገበያ በኩል የሚደረጉ ግብይቶች ላይ የሚታዩ ኢ-ፍትሃዊ የንግድ አሰራሮች ቡናን በብዛትና በጥራት ለገበያ እንዳናቀርብ እያደረገን" ነው ያሉት ደግሞ በደሎ መና ወረዳ በግብይቱ የተሰማሩት አቶ ኡመር ማሙ ናቸው፡፡ በምርት ገበያው በኩል ለተመሳሳይ ቡና የተለያያ የጥራት ደረጃና ዋጋ መስጠት ሌላው የንግዱ ኢ-ፍትሃዊነት የሚገለጽበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በሀረና ወረዳ በግብይቱ የተሰማሩ አቶ ሁሴን ከድር በበኩላቸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባሌ ሮቤ  ላይ እንዲቋቋም በተለያዩ ጊዜያት ቢጠየቅም እስካሁን ባለመፈጸሙ ለከፍተኛ የመኪና ኪራይና እንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ " የምርት ገበያው በዞኑ የሚገኘውን የቡና ምርት እምቅ ሀብት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቅርንጫፉን በአቅራቢያችን እንዲከፍት ሁሉም የሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ተባብረን መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡ የዞኑ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ በሺር በከር በባሌ አካባቢ የሚመረተውን ቡና በብዛትና ጥራት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በምርትና ግብይት ሂደቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ " የዞኑ ዓመታዊ የቡና ምርት ከ15 ሺህ ቶን የሚበልጥ ቢሆንም በ2010 የበጀት ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበው ቡና 1ሺህ ቶን እንደማይሞላና ይህም በዘርፉ ብዙ መሰራት እንዳሚጠበቅብን ትልቅ ማሳያ ነው "ብሏል፡፡ በቡና ግብይት ሂደቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመለየት በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ የንግዱ ማህበረሰብም ቡና ከመሰብሰብ ባሻገር ለጥራቱ መጠበቅ ከአምራች አርሶአደሩ ጋር በቅርበት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ  አቶ ገብሬ ኡርጌሳ በበኩላቸው ህገወጥ የቡና ንግድን ለመከላከል የተጠናከረ ቁጥጥር በማድረግ አጥፊዎቹን ወደ ህግ ለማቅረብ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት መዋቅሮች በኩል  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በኮንትርባንድ ሊሸጥ የነበረ ከ500 ኩንታል በላይ ቅሽርና ጀንፈል ቡና ተይዞ 4 ሚሊዮን ብር   በመሸጥ ለመንግስት ገቢ መደረጉ ህገወጥነትን እየተከላከሉ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ከባለድርሻ አካላት እንዲስተካከሉ የተነሱ ነጥቦችን በግብዓትነት በመውሰድ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራበት ምክትል አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ "በምርትና ግብይት ሂደቱ ውስጥ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትም ለድርድር የማይቀርበውን የጥራት ጥያቄ ማስቀደም አለባቸው "ብለዋል ፡፡ በውይይቱ ከዞኑ የተለያዩ ቡና አብቃይ ወረዳዎች የተወጣጡ በቡና ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡ በባሌ ዞን ከ46 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ምርት እየለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 12ሺህ ሔክታር የሚሆነው ተፈጥሮዊ  የጫካ ቡና እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም