የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ መቋቋሙ የስራ እድል ፈጥሮልናል – የቡልቡላ ከተማ ወጣቶች

850

አዲስ አበባ መስከረም 14/2011 በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ እየተገነባ የሚገኘው የቡልቡላ ኢንቲግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአካባቢውን ወጣቶች በሥራ እድል ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ቀትር ላይ የቡልቡላ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅትም ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ወጣቶች እንደተናገሩት፤ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ በሥራ እድል ተጠቃሚ እያደረጋቸው በመሆኑ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት እንዳስቻለቸውም ገልፀዋል።

የፓርኩ ግንባታ በ263 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን አሁን ባለበት በግንበታ ወቅት ብቻ ከ1 ሺህ 700 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል።

በግንባታ ሥራው ተሳታፊ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ወጣት ለሜቻ በሪሶ፣ አባስ ወርቁ፣ኢንጅነር ለምለም አሰፋ እና ጎሹ አደም፤ በፓርኩ ግንባታ በተፈጠረላቸው የሥራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።

 ስራ በማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል ሌሎችም ትምህርት ጨርሰው ስራ አጥተው የተቀመጡ ወጣቶች እንደኔው  በተፈጠረው እድል ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰተቸውን የተናገረው ለሜቻ በሪሶ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ  ትልቅ የስራ እድል ከግንባታው ወቅት አንስቶ ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል ፈጥሯል የምትለው ኢንጅነር ለምለም አሰፋ ናት፡፡

 “ወላቡ ኮንስትራክሽን” በተሰኘ የአገር ውስጥ የስራ ተቋራጭ እየተሰራ ያለው ይህ ፓርክ በአሁኑ ወቅት ለ1 ሺህ 700 ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ሲጠናቀቅ ከ15 እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

ፓርኩ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ወደ ፋብሪካ ገብተው ተጨማሪ እሴቶች ተጨምሮባቸው ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበት ነው።

በውስጡ 100 ሼዶች ይኖሩታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ እስከ 400 የሚደርሱ ፋብሪካዎች እንደሚይዝም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ ሲጀምር ከሻሸመኔ የገጠር ሽግግር ማዕከል አትክልትና ፍራፍሬ፣ ማር እና የእንስሳት ውጤቶችን በግብዓትነት የሚቀበል በመሆኑ ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ይታመናል።