የኢትዮጵያና የኤርትራን ህዝቦች የማቀራረቡ ሥራ በስነ ጥበብ እንዲደገፍ ጥሪ ቀረበ

138
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 የኢትዮጵያና የኤርትራን ሕዝቦች ለማቀራረብ የተጀመረው ጥረት በሥነ-ጥበብ ስራዎች ሊደገፍ ይገባል ተባለ። ሰለብሪቲ ኢቨንትስ የተሰኘው ድርጅት የሁለቱን አገር ሕዝቦች ለማቀራረብ ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ ለ20ኛ ጊዜ ተካሂዷል። ድርጅቱ የአገሮቹ ሕዝቦች ያጡትን ጉዳዮች እንዴት መመለስ አለባቸው? ህዝቦቹን እንዴት ማቀራረብ ይቻላል? በሚለው ጉዳይ ከዚህ በፊት ከምሁራንና፣ ከሀይማኖት አባቶች ጋር ሰፊ ውይይት እንዲደረግ ማገዙ ይታወሳል። በዛሬው መድረክ ላይ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶችና ደራሲያን የተገኙ ሲሆን የሥነ ጥበብ ሥራዎች የሁለቱን አገሮች ህዝቦች ማቀራረብ በሚቻልበት ሁኔታ ውይይት ተከናውኗል። በእንግሊዝ ኪንግስ ኮሌጅ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአገሮቹ መካከል ሠላም መውረዱ ለሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ አለው። ''ህዝቦቹን ለማቀራረብ ሥነ ጥበብ የላቀ አስተዋዕኦ አለው።'' ያሉት ፕሮፈሰሩ የስነ ጥበብ ባለሙያዎች በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያሉ ስጋቶችና ዕድሎች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። ስነ ጥበብ አንድነት በመፍጠር ረገድ ትልቅ ኃይል እንዳለው ገልጸው በተለይ የግለሰብና የሕዝብ ትረካዎች ላይ ማተኮር ለሚጠበቀው ውጤት ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አስምረውበታል። የውይይቱ ታዳሚ ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም ''በኤርትራ የናፈቅናቸው ሰዎች አሉ እናቴን ሳላያት መሞት አልፈልግም መልካም ነገሮች እንዲፈጠሩ ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ '' ሲል ተደምጧል። አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ በበኩሉ የጥበብ ሰው የፍቅር ሰው መሆኑን ገልጾ፤ 'ባለፈ ጉዳይ መወጋገዝ ተገቢ ባለመሆኑ በቀጣይ አንድነቱ እንዲጠናከር መስራት አለብን' ብሏል። በፊልም፣ በድራማ፣ በግጥምና በሙዚቃ ሥራዎች የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ማቀራረቡ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ አመልክቷል። ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አበራ ሺቢሬ እንደተናገሩት፤ አርቲስቶች የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሁለቱን አገሮች የታሪክ መሰረቶች  ማወቅ ይኖርባቸዋል። ''ይህ እንዲሆን ደግሞ የታሪክ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት አለባቸው'' ሲሉ አቶ አበራ ጠቁመዋል። አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በሰጠው አስተያየት "ኢትዮጵያና ኤርትራ የአንድ እናት ልጆች ናቸው፤ የልጅነት ጓደኞቻችን ተለይተውናል ስሜቱ ከባድ ነበር'' በማለት ገልጾ ህዝቦቹን ለማቀራረብ የድርሻውን ለመወጣት እንደሚሰራ ተናግሯል። በመድረኩ  ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያና የኤርትራ አርቲስቶች በሙያቸው አንድነትን ለመስበክ ቃል ገብተዋል። ከ1991 እስከ 1992 ዓ ም በሁለቱ አገሮች መካከል በተካሄደው ጦርነት በሁለቱም ወገን ቁጥሩ የበዛ የህይወት መስዋዕትነት መከፈሉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም