የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ሚዛናዊነት የጎደለውና እውነታ ላይ ያልተመሰረተ አቋም እንዲያርም ተጠየቀ

101

ጥቅምት 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ሚዛናዊነት የጎደለውና እውነታ ላይ ያልተመሰረተ አቋሙን እንዲያስተካክል ‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ’ የተሰኘ ጥምረት ጠየቀ።

በህዝብ ምርጫ የተመሰረተ መንግስትንና በአሸባሪነት የተፈረጀ ታጣቂ ቡድንን በእኩል ሚዛን ማስቀመጥ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ብሏል።

‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ’ የቤልጂየም ቻፕተር የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ላይ ያስተላለፈውን የውሳኔ ሀሳብ የሚቃወም ደብዳቤ ለፓርላማው የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ዴቪድ ማክአሊስተር አቅርቧል።

የፓርላማው የውጭ ጉዳዮች እንዲሁም የስርዓተ ጾታ ኮሚቴዎች አባላት በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የአገሪቱን እውነት እንዲረዱት ያደርጋል ብለን ጠብቀን ነበር ብሏል።

ይሁንና የአውሮፓ ፓርላማ የኮሚቴዎቹ አባላት የጉብኝታቸውን ግኝት ወደ ጎን በመተው “በትግራይ ክልል የወቅቱ የሰብአዊ እና የሰብአዊ ሁኔታ በተለይም የሕጻናት ሁኔታ” በሚል ያሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት ያለውን አድሏዊ አቋም በግልጽ እንደሚያሳይ አመልክቷል።

የፓርላማው አባላት አሸባሪው ሕወሓት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ጫኝ መኪኖችን በማገትና በቅርቡ የዓለም ምግብ ፕሮግራምን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ በመዝረፍ ለወታደራዊ አላማ መጠቀሙን በውል እንዲረዱት እንደሚፈልግ ግብረ ኃይሉ በደብዳቤው ገልጿል።

ቡድኑ ለትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሚላከውን እርዳታ በመከልከል ሕዝቡን ለችግር መዳረጉን ጠቅሷል።

የአውሮፓ ፓርላማ፣ የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ የሕወሓት ደጋፊዎች ከሚሰጧቸው የተሳሳተ መረጃ ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ተገቢነት እንደሌለው አመልክቷል።

ፓርላማው በኢትዮጵያ ጉዳይ ሚዛናዊና ፍትሐዊ አተያይ ሊኖረው ይገባል ያለው ግብረ ኃይሉ፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግስትንና በአሸባሪነት የተፈረጀ ታጣቂ ቡድንን በእኩል ሚዛን ማስቀመጥ ተቀባይነት የለውም ብሏል።

የሽብር ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በሕዝቡ ግድያ፣ አፈናና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙንና የኢትዮጵያን ሀብት መዝረፉን መገንዘብ እንደሚገባ ገልጿል።

የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ትርጉም ያለው ሚና መጫወት ይችላል ነው ያለው ግብረ ኃይሉ በጻፈው ደብዳቤ።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ችግር ብቸኛ አማራጭ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ብሔራዊ ምክክር በመሆኑ የአውሮፓ ፓርላማ ሰላምን ለማምጣት እየተደረገ ላለው ጥረት ገንቢ በሆነ መልኩ እንዲደግፍ ጥሪውን አቅርቧል።

‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ግብረ ኃይል ኢሮፕ’ የተሰኘው ጥምረት በቤልጂየም፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ስዊዘርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ጣልያን፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ስፔንና ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚያስተባበር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም