ሁሉም ወገን ኢትዮጵያ ከያዘችው እውነት ጎን መሰለፍ ይገባዋል - አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ

308

ጥቅምት 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) ‘ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ’ በሚል መሪ ሃሳብ በመጪዉ ቅዳሜ በሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያ ከያዘችው እውነት ጎን መቆም እንደሚገባ አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ተናገሩ።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከአሸባሪው የሕውሃት ቡድን ጋር በመወገን ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የሚጥሩ አካላትን መቃወም ይገባል ብለዋል።

መንግስት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅና ሉአላዊነቷን ለማረጋገጥ የሄደበትን ርቀት አድንቀው ይህንን መደገፍ ኢትዮጵያን መደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ የውጪ ሀይሎችን ጣልቃ ገብነት ማውገዝ እና ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ አገራትን ማመስገን ያስፈልጋል ብለዋል።

የሕወሃት የሽብር ቡድን ህልውናውን ለማቆየት ሲል የትግራይ ሕዝብን ለከፋ ችግር እየዳረገ መሆኑን አንስተዋል።

ቡድኑ በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና መከራ ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጫና የሚፈጥሩ አካላት በቃችሁ ሊባሉ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያውያን ይህንን በሉአላዊነት ላይ የተጋረጠ መልከ ብዙ ጫና በጋራ ቆመው መመከት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚደግፍ ሰልፍ የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን "ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ መንግስት የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን ጥረት መደገፍ፣ የአንዳንድ የውጪ አገራትን አሉታዊ ጣልቃ ገብነት ማውገዝ እና ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ አገራትን የማመስገን ዓላማ አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም