በበጀት ዓመቱ ከምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎች 148 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል

220

ጥቅምት 10/2015 (ኢዜአ) በዘንድሮው በጀት ዓመት ከምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎች 148 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አስታወቀ፡፡

በምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሻለ አፈፃጸም ላስመዘገቡ ኢንዱስትሪዎች እውቅና ተሰጥቷል።

በአምራች ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዮት የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ በቀለ መኩሪያ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከዘርፉ ከ148 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል፡፡

ከምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፈው በጀት አመት 114 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰው ዘንድሮ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዮት የጨርቃጨርቅና ምግብ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስለሺ ለማ ማዕከሉ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት ያከናወናቸው ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡

በተለይ የስራ እድል በመፍጠር የላቀ ሚና መጫወቱን አስታውሰው ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ከ7 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የተደረገው ጥረት ለውጥ እየታየበት መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ፤ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የምታደርገውን ጉዞ በመደገፍ ረገድ ባለሀብቱ ያለው አስተዋጥኦ የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ "ኢትዮጵያ ታምርት" መርሃ ግብርን በመደገፍና ተሳታፊ በመሆን የኢትዮጵን ብልጽግና ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ባለሀብቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዝግጅቱ ለሴት ባለሀብቶች፣ አምራቾች፣ በኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ለተሰማሩና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የዕውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም