“ከምንሸጠው ቆሻሻ የምናገኘው ጥቅም ዝቅተኛ ነው፤ ቆሻሻ የምናከማችበትና የምንለይበት ቦታ ችግርም አለብን” -ማህበራት

102
ግንቦት 11/2010 በመዲናዋ ደረቅ ቆሻሻ ሰብስበው እየለዩ የሚሸጡ የሽርክና ማህበራት ቋሚ የማከማቻና መለያ ቦታ ችግር እንዳጋጠማቸውና ከሽያጩ የሚያገኙት ገቢም ከድካማቸው ጋር እንደማይመጣጠን ገለጹ፡፡ የደረቅ ቆሻሻ መልሶ መጠቀም ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ የቦታ ችግሩን ለመቅረፍ "እየሰራሁ ነው" ብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ስድስት ሺህ ያህል አባላትን ያቀፉ 600 የጽዳት ማህበራት በ74 የሽርክና ማህበራት ተደራጅተው ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሃብት በመቀየር ስራ ተሰማርተዋል፡፡ ደረቅ ቆሻሻ በመሰብሰብና መለየት  ከተሰማሩት የሽርክና ማህበራት መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የአዲስ ህይወት ሽርክና ማህበር አንዱ ነው። የማህበሩ ኮሚቴ አባል አቶ ሄኖክ ደግፍ እንዳሉት በስሩ ከሶስት ወረዳዎች የተውጣጡ 147 ኣባላትን ያቀፈው ማህበራቸው ደረቅ ቆሻሻዎችን ለይቶ ለአምራቾች ይሸጣል፡፡ ማህበሩ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለሚያውሉ ድርጅቶች ከሚያቀርባቸው ደረቅ ቆሻሻዎች መካከል የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ የብረት ቁርጥራጮች፣ ካርቶን፣ ወረቀቶች እና ሌሎች ይገኙበታል። ሽርክና ማህበሩ የተሻለ ስራ እየሰራ ቢሆንም የክፍያ አለመመጣጠንና የቦታ ችግር ለስራው እንቅፋት እንደሆኑበት አቶ ሄኖክ ተናግረዋል፡፡ የማህበሩ አባል ወይዘሮ ዓለም ቴዎድሮስ እንዳሉት በየመንደሩ ተንከራተው ሰብስበውና ለይተው ለሽያጭ ከሚያቀርቡት ደረቅ ቆሻሻ የሚያገኙት ገቢ ወርሃዊ ወጪያቸውን በቅጡ አይሸፍንላቸውም፡፡ ሪፖርተራችን በመዲናዋ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የሌሎቸ ማህበራት አባላትም ሰብስበውና ለይተው ከሚሸጡት ቆሻሻ የሚያገኙት ገቢ ከድካማቸው ጋር የተመጣጠነ አለመሆኑ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡ ቋሚ የደረቅ ቆሻሻ  ማቆያና መለያ ማዕከላት አለመኖርም የስራ እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ መልሶ መጠቀም ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት የመልሶ መጠቀምና ኡደት ዳይሬክተሩ አቶ ካሳሁን ፀጋዬ እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ ማህበራቱ ከክፍያ ጋር በተያያዘ የሚያነሱትን ቅሬታ ለመፍታት በሚሸጡት አንድ ኪሎ ግራም ቆሻሻ ላይ የሁለት ብር ድጎማ ያደርጋል፡፡ ማህበራቱ የሰበሰቡትንና የለዩትን የፕላስቲክ ጠርሙስ አንዱን ኪሎ ግራም በሶስት ብር ሲሸጡ ከተማ አስተዳደሩ በእያንዳንዱ ኪሎ ግራም ላይ የሁለት ብር ድጎማ ያደርግላቸዋል፡፡ ማህበራቱ የሚያነሱትን የቆሻሻ ማቆያ ቦታ እጥረት ለመፍታት ደግሞ  ለእያንዳንዳቸው 500 ካሬ ሜትር ቦታ ለመስጠት በከተማ አስተዳደሩ መወሰኑን ነው ዳይሬክተሩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የገለጹት። እስካሁንም 31 ቦታዎች ተለይተው ለክፍለ ከተማ ፅዳት ፅህፈት ቤቶች መተላለፋቸውን ያብራሩት ዳይሬክተሩ በተመረጡ ቦታዎች ግንባታ ለመጀመር የአማካሪ ጨረታ መውጣቱን ተናግረዋል። ደረቅ ቆሻሻ ሲያስወግዱ የነበሩ ማህበራት ቆሻሻ ሀብት መሆኑን እንዲገነዘቡ በማድረግ በ2009 ዓ.ም በከተማዋ ከተለየው ደረቅ ቆሻሻ 36 ሚሊየን ብር ተገኝቷል። በተያዘው በጀት ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከቆሻሻ ሽያጭ ከ47 ሚሊየን ብር በላይ  መገኘቱንም  አቶ ካሳሁን ገልጸዋል። በዚሁ ጊዜ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል  ወደ ውጪ ከተላኩ ምርቶች ደግሞ  ከ1 ሚሊየን 300 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። እስከ በጀት ዓመቱ ሶስተኛ ሩብ ዓመት ድረስ ብቻ ከ844 ሺህ ቶን በላይ ቆሻሻ መወገዱንና 31 ሺህ ቶን ደረቅ ቆሻሻ ደግሞ ለመልሶ ጥቅም አገልግሎት ወደ ሃብትነት መቀየሩን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም