የተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤቱ የባለ ልዩ ተሰጥኦ ሰዎችን ሀሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ ትልቅ አቅም ይፈጥራል

176

ጥቅምት 10/2015 (ኢዜአ) የተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤቱ የባለ ልዩ  ተሰጥኦ ሰዎችን ሀሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት፤ ሁሉም ሰው የማያልቅ ተሰጥኦ ቢኖረውም ከብዙዎቹ መካከል ደግሞ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው እንዳሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም ባለተሰጥኦ ሰዎች ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ በአዕምሯቸው ያላቸውን ሀሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደሚቸገሩ ገልፀው፣ አማራጭ የተሰጥኦ ትምህርት ቤት ማስፍለጉን ጠቅሰዋል።

ቡራዩና አካባቢው ውብ የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለ እንደሆነ ገልፀው፣ ሁሉም ባለተሰጥኦ ልጆች ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ወደ ትምህርት ቤቱ መላክ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያቆም የለም፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ችግርም ሰላም ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፕሮጀክቱ ስኬት የተጉ አካላትንም አመስግነዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ  በበኩላቸው ትልቁ ድህነት የአዕምሮ ድህነት መሆኑን ገልጸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጭነት የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ወደ ተግባር የመለወጥ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተገነቡ ያሉ ማእከላትም የኢትዮጵያ ልጆች አዕምሮ በልጽጎ ወደ ሀብት የሚለወጥበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ በበኩላቸው የተመረቀው ተቋም የወደፊቷ ኢትዮጵያ ተስፋ የሆኑ ባለተሰጥኦ ማፍሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

ህዝብና አገር ለማገልገል ሃላፊነት ከወሰዱ በኃላ ከተረከቧቸው ቁልፍና ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተቋሙ ወጣቶችን በማስተማር ውጤታማ መሆናቸውን አውስተው፣ ባለተሰጥኦዎችን ማፍራት ላይ ይሰራል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተቋሙ ሃላፊ እያሉ የተጠነሰሰና በብዙ ፈተናዎች ያለፈ ፕሮጀክት ስለመሆኑም አስታውሰዋል።

በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት የተሻለ ሀሳብና ተሰጥኦ ላላቸው ልጆች ትልቅ ብስራት መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም