የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናትን ከጉዳት ለመጠበቅና ለማደስ የሚያስችል የአምስት ሚሊዮን ዩሮ የእርዳታ ስምምነት ተፈረመ

101

ጥቅምት 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መንግስት መካከል የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናትን ከጉዳት ለመጠበቅና ለማደስ የሚያስችል የአምስት ሚሊዮን ዩሮ የእርዳታ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው፤ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ እና የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ዳይሬከተር ቫሌሪዬ ቴሂኦ ጋር ተፈራርመዋል።

ድጋፉ ለላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እድሳት እና እንክብካቤ የሚውል መሆኑ ተመላክቷል።

የእርዳታ ስምምነቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከአራት አመት በፊት ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በተወያዩበት ወቅት ሁለቱ አገራት በቅርስ ጥበቃ ረገድ ትብብር ለማድረግ መግባባት ላይ በደረሱት መሰረት ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮጀክት አካል መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቅርሶች በማሳደግና በማልማት የጎብኚ ቱሪስቶችን ፍሰት የሚጨምርና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ የማሳደግ አላማ እንዳለውም እንዲሁ።

በተጨማሪም ለአካባቢው ማህበረሰብ ተጨማሪ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን የሚውል ነው።

እንዲሁም ህንጻዎቹ በቀጣይ እንዳይበላሹ አስፈላጊውን የመከላከል ስራ ለመስራት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፈረንሳይ መንግስት በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያካበተ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ እድሳቱ ይህንኑ ልምድ ለመቅሰም እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናትን ለመንከባከብ እና ለቅርሱ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደሩ፤ ባህልና ቅርስን በተመለከተ በትብብር መስራት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ድጋፉ ላልይበላን ከጉዳት ለመጠበቅና የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለማሳደግ ያግዛል ያሉት ደግሞ የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ቫሌሪዬ ቴሂኦ ናቸው።

እንዲሁም በቀጣይ መንግስት ቅርሶችን ለመጠበቅ ለሚያከናውናቸው ስራዎች አጋዥ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም