ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቡራዩ ከተማ የተገነባውን የተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት መርቀው ከፈቱ

177

ጥቅምት 10/2015 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቡራዩ ከተማ የተገነባውን የተሰጥኦ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት መርቀው መክፈታቸው ተገለጸ፡፡

በመደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በማሰልጠኛ ተቋማትና በኢንተርፕራይዞች የወጣቶችን ተሰጥኦ የማጎልበት ስራ ማከናወን አስፈላጊ ነው።

አሁን ባለው እውነታ ወጣቶቹ ተሰጧቸውን አበልጽገው ወደምርትና አገልግሎት ለመቀየር ከፈለጉ የትምህርት ስርዓቱ የሚፈልገውን ቆይታ ማጠናቀቅ ግድ ይሆንባቸዋል።

ወጣቶቹ የሚያጋጥማቸውን ውጣ ውረድ ማለፍ ሲሳናቸው ደግሞ ተሰጥኦዋቸውን ለመረዳት ፤ለማውጣትና ለመተግበር ስለሚቸገሩ ባክነው የሚቀሩበት እድል ሰፊ ነው።

በመሆኑም ከመደበኛው መማር ማስተማር ሳይለዩ ተሰጧቸውን ያለጊዜ ገደብ ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲለወጡና አገር እንዲጠቅሙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ይነገራል።

የተገነባው ማዕከልም በአገራዊ ለውጥ ምክንያት በነበሩ ጫናዎች ውስጥ ሆኖ መጠናቀቁና የአካባቢው ህዝብ በግንባታ ሂደቱ ንብረት እንዳይጠፋና እንዳይባክን ጠብቆ ለምረቃ ያበቃው መሆኑ ተገልጿል።

የአካባቢው ነዋሪ ከመሬት ስጦታ እስከ ጉልበት ያለምንም ካሳ አስተዋጽኦ ያደረገበት በመሆኑ ህዝብ ከተባበረ ምንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑም ተመልክቷል።

የማዕከሉ መገንባት አዲስ ከተማ ከመፍጠር ባለፈ ከትምህርት፣ ከሰው ኃይል ልማትና ከስራ እድል ፈጠራ፣ ከሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማትና ምርምር አኳያ መሠረት ይጥላል ተብሏል።

በአንድ ጊዜ 1 ሺህ ባለተሰጥኦ ወጣቶችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችለው ትምህርት ቤቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ 500 ሰልጣኞችን የሚያስተናግድ ይሆናል።

የፕሮጀክቱ ተጨማሪ ማስፋፊያ ሲገነባ በ10 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን ዛሬ የተመረቀው በ4 ነጥብ 3 ሄክታር መሆኑ ታውቋል።

በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያ ነው የተባለው ማእከል የመመገቢያ አዳራሽ፣ የአስተዳደር ሕንጻ፣ የሕክምና ማዕከል፣ የመማሪያ ክፍሎችና የጋራ መማሪያ አዳራሽ እንዲሁም ቤተ ሙከራን የያዘ ዘጠኝ ብሎክ ህንፃ ያለው መሆኑ ታውቋል።

በተጨማሪም ኤሌክትሮ መካኒካል፣ የኬሚካልና ዲጅታል፣ ወርክሾፖች፣ ቤተ መጻህፍት እና ተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን ያሟላ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ለትምህርት ቤቱ የተሟሉት ቁሳቁሶቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ እንደሆኑም ተመልክቷል።

ፕሮጀክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጠንሳሽነት የተጀመረና በእርሳቸው ጥብቅ አመራር የተፈጸመ መሆኑ ታውቋል።

በዚሁ አጋጣሚ ለአካባቢው ሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ፣ የጎዳና እና የውስጥ ለውስጥ መብራትና የውሃ አገልግሎት ማቅረብ ማስቻሉም ተመላክቷል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መሠረቱ ተጥሎ ስራው የተጀመረው በ708 ሚሊዮን 693 ሺህ ብር መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም