የምዕራብ አርሲ ዞን ነዋሪዎች በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከቡ ነው

113

ሻሸመኔ ጥቅምት 9/2015(ኢዜአ) በምዕራብ አርሲ ዞን በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ እያከናወኑ እንደሆነ የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢዜአ ችግኝ ሲንከባከቡ ያገኛቸው የዞኑ ወንዶ እና ሲራሮ ወረዳ ነዋሪዎቹም ችግኝ አስፈላጊ እንክብካቤ ካላገኘ አይጸድቅም ብለዋል።

የወንዶ ወረዳ ነዋሪው አቶ ከድር ጉታ በዘንድሮ አረንጓዴ ዓሻራ መርሀ ግብር አቮካዶን ጨምሮ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች መትከላቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ችግኞች ጸድቀው ጥቅም እንዲሰጡ የመንከባከብ ስራውን አዘወትረው እየሰሩ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

የሲራሮ ወረዳ  ነዋሪው አቶ መሀመድ አብዱ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንና አሁንም በችግኝ እንክብካቤ የተሻለ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

''ችግኝ መትከልና መንከባከብ የአካባቢ ስነ ምህዳርን ለመጠበቅና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ ነው'' ያሉት ደግሞ የምዕራብ አርሲ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኢብሳ  ገመዳ ናቹው።

በዘንድሮ አረንጓዴ ዓሻራ መርሀግብር ከ232 ሚሊየን በላይ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውንና 31 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ለምግብነት የሚውሉ ናቸው ብለዋል።


ባለፈው ዓመት ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 74 በመቶ መጽደቁንም ሀላፊው አብራርተዋል።

''የዞኑ ህዝብ ደንን በመንከባከብ ከካርቦን ሽያጭ ገቢ ማግኘት መጀመሩ ሕዝቡን አነሳስቶታል'' ያሉት ምክትል ሃላፊው ህዝቡ ችግኝ ከመትከል ባለፈ እንክብካቤ በማድረግ ከደን የሚያገኘውን ጠቀሜታ እንዲያሳድግም አስገንዝበዋል።


በዚህም ደንን በአግባቡ የተንከባከቡ የዞኑ ነዋሪዎች በካርቦን ሽያጭ ከ35 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም