ስኬቶችን በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ጉዞ መረጋገጥ የፖለቲካ አመራሩ የመሪነት ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል - ጽ/ቤቱ

155

ሰመራ፣  ጥቅምት 8/2015 (ኢዜአ) ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችን በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ጉዞ መረጋገጥ የፖለቲካ አመራሩ የመሪነት ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲል በብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

"በደም የተከበረ ክብር በላብ ማነጽ" በሚል መሪ-ቃል የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉበት የሁለት ቀን የምክክር መድረክ ዛሬ በሠመራ ከተማ ተጀምሯል ።

በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢሴ አደም እንደገለጹት፤ ባለፉት አመታት የሽብር ቡድኑን ሀገር የማፍረስ ሴራን ከመቀልበስ ጎን ለጎን በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በወጪ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ ልማት፣ በግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት እንዲሁም ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነትን በመከላከል አበረታች ስኬቶች መገኘታቸውን አመልክተዋል።

በተለይም በክልሉ የሽብር ቡድኑን ወረራ ከመመከት ጎን ለጎን በመደበኛ የልማት ሰራዎች፣ በእንሳት ሃብት ልማትና ግብርና እንዲሁም በማእድን ልማትና በገቢ ሴክተሩ የተመዘገቡ አፈጻጸሞች ስኬታማ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

የክልል መንግስትና ህዝብ የሽብር ቡድኑ በሀገርና በክልሉ ላይ የደቀነውን ተጨባጭ የህልውና አደጋ በመቀልበስ ሚናቸውን መወጣታቸውን ጠቁመው፤ አመራሩ ህብረተሰቡን አስተባብሮ በአግባቡ በመምራት ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወቱን አውስተዋል።

በሌላ በኩል የሽብር ቡድኑን ወረራ በመመከት ከተመዘገቡ ድሎች በተጨማሪ በጦርነቱ ዙሪያ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ረገድ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የገጠመንን ፈተና ወደ መልካም እድል በመቀየር ስለሽብር ቡድኑ ቀሪው አለም የነበረውን ብዥታና ተያያዥ የተሳሳቱ አረዳዶች በማረም በዲፕሎማሲው መስክ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በየደረጃው ያለው የክልሉ የፖለቲካ አመራር በቀጣይ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በዲፕሎማሲ መስክ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ጉዞ መረጋገጥ የመሪነት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም