ለመከላከያ ሠራዊት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

145

መተማ፣ ጥቅምት 8/2015 (ኢዜአ) የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የስንቅና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊና ሎጅስቲክ አስተባባሪ ወይዘሮ ብርሃን ንጉሴ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንዳሉት፣ ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ከከተማ አስተዳደሩና ከነዋሪዎች የተውጣጣ ነው።

በድጋፉ የእርድ እንስሳት፣ በሶ፣ ስኳር፣ ጁስ፣ ውሃና ሌሎች ቁሶች መካተታቸውን የገለጹት አስተባባሪዋ፣ "ህወሓት ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት ከከፈተ ወዲህ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ሲያደርግ ለ2ኛ ጊዜ መሆኑን ገልፀዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ህዝብ በቀጣይም የደጀንነት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የጤና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ክሽን ወልዴ በበኩላቸው፣ "አሸባሪውን ህወሓት እየመከተ ላለው የመከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር አለበት" ብለዋል።

በአካባቢው የሽብር ቡድንና ፅንፈኛ ኃይሎች ተደጋጋሚ ትንኮሳ ቢያደርጉም በወገን ጦር የተቀናጀ ስራ ማምከን መቻሉን ተናግረዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዛሬ ያደረገው ድጋፍ በግንባሩ ላለ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆን ጠቅሰው፤ "መሰል የደጀንነት ስራም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።

ድጋፉን የተረከቡት ሻለቃ ኢሳያስ ጌታቸው በበኩላቸው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች ያደረጉት ድጋፍ በሌሎች የከተማ አስተዳደሮችና ድርጅቶችም ሊደገም እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ለሠራዊቱ ተጨማሪ ወኔና ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ መሆኑንም ሻለቃ ኢሳያስ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም