ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግጭቶችን ለመቀነስና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚረዱ ፕሮጀክቶች ይካሄዳሉ-ሚኒስቴሩ

73

ሀዋሳ፣ ጥቅምት 8 ቀን 2015 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመቀነስና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው ሀገራዊ " የ10 ዓመት የዘላቂና ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ ፕሮግራም " ላይ ከደቡብና ከሲዳማ ክልል ከተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ውይይት ተደርጓል።

በውይይት መድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስትር አማካሪ አቶ ሰውነት ቸኮል እንደገለጹት ሚኒስቴሩ ከ2015 እስከ 2019 ዓም ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ሥርዓት ፕሮጀክት ቀርጿል።

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ለሚጠበቀው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከ2 ቢሊዮን 220 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ወጪው በመንግሥት፣በህዝብና በልማት አጋር ድርጅቶች ተሳትፎ እንደሚሸፈን አመላክተዋል ።

"በፕሮጀክቱ በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶች ወደ ብጥብጥ ከመሸጋገራቸው በፊት ቀድሞ ለመከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጠንካራ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ሥርዓት ለመዘርጋት ይሰራል" ብለዋል።

በተለይ የኢጋድ እና የአፍሪካ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት ልምድን በመቅሰም ስራ ላይ ለማዋል ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

"አሁን ላይ የአስተዳደር ወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች የግጭት መንሰዔ እየሆኑ ነው" ያሉት አቶ ሰውነት "ችግሩን ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አስራር ይዘረጋል"።

በሀገሪቱ የግጭት መንስኤዎችን በጥናት በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ በቅንጀት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

ፕሮጀክቱ ግጭቶችን በመከላከል የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት በማስጠበቅ ልማትና እድገትን ለማፋጠን ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

በሰላም ግንባታ ዙሪያ በትብብርና በቅንጀት የመስራት አቅምን ለማጎልበት ፕሮጀክቱ ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል።

"ህዝቡ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዝ ፕሮጀክት በመሆኑ ዘላቂነት እንዲኖረው ይደረጋል" ብለዋል።

በተመሳሳይ በ8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ ሰላምና ህብረ ብሄራዊ አንድነት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮጀክት በሀገሪቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለጸት ደግሞ ሌላኛው የሰላም ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር እሸቱ ደሴ ናቸው።

እንደሳቸው ገለፃ ከዚህ ዓመት አንስቶ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚቆየው ፕሮጀክት ተግባራዊ የሚደረገው በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ነው።

"በሀገሪቱ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት አለመገንባቱ ለፕሮጀክቱ መነሻ ተደርጎ ተወስዷል" ያሉት አምባሳደሩ ችግሩን ለመቀልበስ ሚኒስቴሩ አዲስ ፕሮጀክት መቅረጹን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ አገራዊ አንድነትንና ማህበራዊ ትስስርን በማስፈን ብሔራዊ መግባባት በማስረፅ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የጎላ አስተዋጾ እንዳለው አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና አላማም በጎ ፈቃደኝነት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ማዋል፣ተቋማዊ የማስፈጸም አቅምን ማሳደግ መሆኑን አመላክተዋል።

እንደ አምባሳደር እሼቱ ገለፃ የወጣቶችን የስራ ባህልና ክህሎት የማሳደግና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል መፍጠር ተጓዳኝ አላማ ያለው ፕሮጀክት ነው።

"ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆን የዜጎች የሀገር ፍቅር፣መተሳሰብና የመረዳዳት ጠቃሚ ባህል ይበልጥ የሚጎለብትበት እንዲሆን ይጠበቃል" ሲሉ አመላክተዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርሰቱ ይርዳው እንዳስታወቁት ከሰላም በላይ ቅድሚያ ሰጥተን የምናከናውነው ስራ የለም ።

"ባለፉት ዓመታት በሀሰተኛ ትርክት እና በብሄር መከፋፈል ምክንያት ሰላማችን እየተናጋ ስንቆስል መቆየታችን ሊያበቃ ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

"የሰላም ግንባታ ሁሌም የሚኮተኮትና የሚሰራ ነው" ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ከዚህ አንፃር በሚኒስቴሩ የተዘጋጁ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ፍሬያማ እንዲሆኑ የክልሉ መንግሥት የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳደር ተወካይ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ "ከአደረጃጀት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተከሰተው የሰላም እጦት የክልሉ ህዝብ ዋጋ ከፍሏል" ብለዋል።

በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች፣ የፀጥታ መዋቅሮችና በመላው ህዝብ ጥረት በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ጠቅሰው "በሚኒስቴሩ የተዘጋጀው የሰላም ግንባታ ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለመንከባከብ ይረዳል" ብለዋል።

አሁን ላይ እየተስፋፋ የመጣውን ድህነት እና ስራ አጥነት ችግር ለማቃለል እና የስራ ባህልን ለማዳበር በሚኒስቴሩ የተቀረጸው የሰላምና ህብረ ብሄራዊ አንድነት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮጀክት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ስላለው ለተፈጻሚነቱ የክልሉ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

ለአንድ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ከሚኒስቴሩና ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም