በጎንደር፣ በባህር ዳርና ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲዎች ከ43 ሺህ በላይ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናቸውን እየወሰዱ ነው

106

ጎንደር/በባህርዳር/ድሬዳዋ/ሀረር፣ ጥቅምት 8/2015 (ኢዜአ) በጎንደር፣ በባህርዳርና ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲዎች ከ43 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሁለተኛውን ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተናቸውን ተረጋግተው እየወሰዱ መሆኑን ዩኒቨርሲቲዎቹ አስታወቁ፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ፈተናው እየተሰጠ ያለው በዩኒቨርሲቲው ለመፈተኛ በተዘጋጁ 5 ካምፓሶች ነው።

በፈተና ሂደቱ ከ900 በላይ መምህራንና የፈተና አስተባባሪዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ተማሪዎችም ፈተናውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተረጋግተው እየወሰዱ መሆኑን ገልፀዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው የሁለተኛውን ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ከ23 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈታኞች ፈተናውን ተረጋግተው እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመው፤ በመጀመሪያው ዙር የተፈጠረው ዓይነት መጠነኛ ችግር እንዳይከሰት ለተማሪዎቹና ለወላጆቻቸው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሰራቱንም አስረድተዋል።

የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ የትምህርት ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር መገርሳ ቃሲም በዩኒቨርስቲው 5 ሺህ 329 ተማሪዎች ሁለተኛውን ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና በተረጋጋ ሁኔታ እየወሰዱ እንደሚገኙ ተናግረው፤ ፈተናው ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።

ተፈታኝ ተማሪዎቹ ጎንደር ከተማን ጨምሮ ከማዕከላዊ እና ከምዕራብ ጎንደር ዞኖች የመጡ መሆኑንም ዶክተር ካሳሁን አመልክተዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛው ዘር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲው ዋና ካምፓስና ሐረር ከተማ  በሚገኘው የጤና እና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ  ከ9 ሺ በላይ ተማሪዎች ለፈተና ተቀምጠዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ ተማሪዎች   እንዳለፈው ዙር ፈተና አሁንም በተረጋጋ መንፈስ  በመፈተን ላይ እንደሚገኙ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ ዩኒቨርሲቲዎቹ በመጀመሪያ ዙር የ12ኛ ክፍል ፈተና የታዩ ጥቃቅን ክፍተቶችን አርመው ሁለተኛውን ዙር የፈተና ሂደት የተሳካ ለማድረግ ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

በመጀመሪያው ዙር የ12ኛ ክፍል የማኅበራዊ ሳይንስ ፈተና ዩኒቨርሲቲዎቹ ከ70 ሺህ 488 ተማሪዎች በላይ ኢዜአ መዘገቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም