የካፊቾ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በቦንጋ ከተማ እየተከበረ ነው

157
ሚዛን መስከረም 13/2011  የካፊቾ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል "ማሽቃሮ" በዞኑ ዋና ከተማ ቦንጋ በድምቀት እየተከበረ ነው። የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማስረሻ በላቸው በበዓሉ ላይ እንዳሉት የካፊቾ ብሔር የዘመን መለወጫ ማሽቃሮ ሁሉንም የሚያሳትፍ የአብሮነት ማሳያ ነው። በዓሉ ከትውልድ ወደትውልድ ሲተላለፍ የቆየ አስተዳደራዊ ዕሴት ያለው መሆኑንም ተናግረዋል። "በዓሉ የተጣሉ እርቅ የሚያወርዱበትና ሰላም የሚያሰፍኑበት በመሆኑም ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ ነው" ብለዋል። በበዓሉ ልዩ ልዩ ጠቃሚ አስተዳደራዊ ዕሴቶች እንዳሉት የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ በቀጣይ ባህሉን በተገቢው ሁኔታ የመጠበቅ፣ የማልማትና የማበልጸግ ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል። የበዓሉ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አቶ ደስታ ገነመ በበኩላቸው የካፊቾ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ከብሔሩ ባህላዊ መገለጫ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል። በበዓሉ ላይ መገኘታቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸውና በዓሉ የህዝቡን አንድነት በማጠናከር በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። ከውሽውሽ የመጡት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ገብሩሽ አበበ በበኩላቸው "የበዓሉ አከባበር የጥንቱን ባህላዊ አስተዳደራዊ ጥንካሬ የሚያሳይ ነው" ብለዋል፡፡ የብሔሩን ጠንካራ እሴቶች ለወጣቱ ለማስተላለፍ ዞኑ በትኩረት መስራት እንዳለበት ገልጸው በዓሉ እየተከበረ ያለበትን "ቦንጌ ሻንበቶ" አካባቢን በማልማት የቱሪስት መስህብ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ የካፋ ንጉስ መቀመጫ በሆነውና በየዓመቱ በዓሉ በሚከበርበት "ቦንጌ ሻንቤቶ" በሚባለው ስፈራ በዓሉ ሲከበር በዞኑ የሚኖሩ ብሔረሰቦችን ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያሳይ ስነ ስርዓት ያካሂዳሉ፡፡ በበዓሉ በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ የዞኑና አካባቢው ተወላጆች፣ ምሁራንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች ተገኝቷል። እስከ ነገ በሚቀጥለው የበዓል አከባበር ላይ በባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው የፓናል ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን በዓሉ እየተከበረ ባለበት ስፍራም የባህል ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም