በደቡብ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተተከሉ ችግኞች የክልሉ የደን ሽፋን አድጓል--ቢሮው

155

ሆሳዕና፤  ጥቅምት 8 ቀን 2015 ( ኢዜአ) በደቡብ ክልል ባለፉት አራት ዓመታት በተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የክልሉ የደን ሽፋን 16 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን የደቡብ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የደቡብ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ ልማት ሥራ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካትና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስተዋጾው የጎላ ነው።

በልማቱ ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ምክንያት የሆኑ የደን መራቆትና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።  

"በእዚህም የዜጎች ጤናና ደህንነት ተጠብቆ የመኖር መብታቸውን ለማስጠበቅ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በተሰሩ የችግኝ ተከላ ሥራዎች 15 ነጥብ 5 በመቶ የነበረው የክልሉ የደን ሽፋን ወደ 16 ነጥብ 7 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ነባርና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር የሚያግዙ እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን በመሸፈን ለኑሮ ምቹ አካባቢን ለመፍጠር ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ ዳንኤል የገለጹት።

በአረንጓዴ ልማቱ ከችግኝ ተከላ ጀምሮ እስከ ጥበቃ ድረስ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው፣ በቀጣይ ዘርፉን የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የክልሉን የደን ሽፋን ወደ 23 በመቶ ለማሳደግም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም አመልክተዋል።

"የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው በየአካባቢው የሚስተዋለውን የንፅህና ጉድለት ችግር በመፍታት ምቹ አካባቢ ለመፍጠርና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ እንደ አመራር ከፊት ሆነን ሚናችንን መወጣት አለብን" ብለዋል።

"የደን ልማት ሥራን በማጠንክር የአየር ንብረት ለውጥን መቆጣጠር ከማንኛውም ተግባር ቀዳሚ አድርገን ልንሰራ ይገባል" ሲሉም ጠቁመዋል።

በዕቅድ ግምገማ መርሃ-ግብሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ባዩሽ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የዞንና የወረዳ የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም