ሁለተኛው ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሁሉም አካባቢዎች በተሳካ ሁኔታ በመሰጠት ላይ ነው- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

174

ጥቅምት 08/2015(ኢዜአ) የሁለተኛው ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሁሉም አካባቢዎች በተሳካ ሁኔታ በመሰጠት ላይ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ሚኒስትር ዴታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወሳጅ ተማሪዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም ተማሪዎች በተረጋጋ ሁኔታ ፈተናውን እየወሰዱ እንደሚገኙና ይህም በመጀመሪያው ዙር የታዩ ድክመቶችን በማሻሻል ለሁለተኛው ዙር የተሻለ ዝግጅት በመደረጉ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

እንደ አጠቃላይ ሁለተኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና በሁሉም አካባቢዎች በተሳካ ሁኔታ በመሰጠት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸው በተለይም ወላጆች፣ ተማሪዎችና አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ እያደረገ ያለውን ትብብርና ድጋፍ አድንቀዋል።

በሁለተኛው ዙር የፈተና መርሐግብር ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን በ130 የፈተና ጣቢያዎች በሙሉ ፈተናው መሰጠት መጀመሩ ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም