የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ በኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ዘንድ መነቃቃት ፈጥሯል

1031

አዲስ አበባ መስከረም 13/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ ከዳያስፖራዎች ጋር ያደረጉት ውይይት በአገራቸው የተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ  የበለጠ መነቃቃት እንደፈጠረባቸው  ዲያስፖራዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ባላቸው እውቀትና አቅም በአገራቸው ውስጥ በተለያዩ መስኮች እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ወደ አገራቸው ተመልሰው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ መነቃቃት እንደፈጠረባቸ ነው የተናገሩት።

በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች በመሰማራት ለአገራቸው እድገትና ብልጽግና የበኩላቸውን ለማበርከት ያላቸውን ዝግጁነትም ገልጸዋል።

የካናዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ሰለሞን እናዳሉት ˝ለአገራችን ምን ብንሰራ ጥሩ ነው የሚለውን የዛን አገር ልምድ ቀስመን በዚህ አገር ላይ  ላደርግ የማስባቸው  ነገሮች አሉ ፤ በቆይታዬ   በአዳማ ሆስፒታልና በጳውሎስ ሆስፒታል ካሉ ሰዎች ጋር አንዳንድ ነገሮችን ለማድረግ የጀመርኩት  አለኝ  በዛ ላይ ነው በአገሪቷ ላይ ልሰራ የምፈልገው ”

“ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ ከመጡ ወዲህ ወደ አገር ቤት መጥቶ የመስራት ፍላጎቴን ጨምሮታል አሁንም መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ፤ ብዙ ሰዎች ወደ አገራቸው መጥተው ያላቸውን ካፒታል እዚህ ኢንቨስት አድርገው ራሳቸውንም አገራቸውንም መጥቀም የሚፈልጉ አሉ፤ እኔም ከእነሱ ውስጥ አንዱ ነኝ  ያሉት ደግሞ  ከአሜሪካ የመጡት  አቶ ሳሙኤል ዋቅጅራ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር በበኩሉ ወደ አገራቸው መጥተው ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ቁጥር እየጨመረና የበለጠ መነቃቃት እየታየ መሆኑን ገልጿል።

የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም እንደገለጹት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን አሜሪካ ከዲያስፖራው ጋር ያደረጉት ውይይት መነቃቃትና አገራዊ አንድነትን የፈጠረ ነው።

በቀረበው ጥሪ መሰረት ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው መጥተው በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች መስኮች በመሳተፍ ለአገራቸው የሚፈለግባቸውን ሚና ለመወጣት እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።

ማህበሩ በአገራቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሳተፍ የሚፈልጉ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትን መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ስለ አገራቸው ነባራዊ ሁኔታ የማስገንዘብና የመደገፍ ስራውን ያጠናክራል ነው ያሉት።

እየተፈጠረ ባለው መነቃቃት በቀን በአማካይ ከ15-20 የሚደርሱኑ ዳያስፖራዎች በማህበሩ በኩል በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።