"ልዩነት አልባ ጦርነት"

98
ነጻነት አብርሃም (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለዘመናት ታፍራና ተከብራ የኖረች ታላቅ አገር ናት። የኩሩና የታላላቅ ህዝቦች እንዲሁም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ታሪኮች ባለቤትም ጭምር። ድሮ ድሮ ስለ ሰላም፣ ስለ መከባበርና ስለመቻቻል ሲወራ ልዩነቶች በሌሉበት አንድነት አብሮ በፍቅር የሚኖር ህዝብ እና አገር ባለቤት የሆነች አገር ኢትዮጵያ መሆኗንም የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። አንድነቷ የጠነከረ አገርና ልጆቿም ልዩነቶቻቸውን ውበት አድርገው የኖሩ ናቸው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን እነዚህ አገራዊ እሴቶች ቀስ በቀስ እየተሸረሸሩ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያፈነገጡ ድርጊቶች እዚህም እዚያም ሲሰሙ ተስተውለዋል። ይህ ብቻ አይደለም አገርን እንደ አገር ለማስቀጠል አደጋ የሚፈጥሩ ህዝባዊ ቁጣዎች ተስተውለው እንደነበር ባለፉት ጊዜያት ማየት ችለናል። በእርግጥ ህዝቦች የተለያዩ ጥያቄዎች የነበሯቸው ሲሆን ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ይሰጥባቸው ዘንድ ደረጃ በደረጃ የተኬደበት መንገድ ነበር። በሂደቱም ነገሮች ፈር እያጡ ሲመጡ በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለመፍትሄው አንድ አካል እሆን ዘንድ በማለት ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው አስረክበው ለብዙ አፍሪካዊያን መሪዎች ማስተማሪያ የሆነ ኃላፊነትና ጨዋነት የተሞላበት ተግባር በመፈጸም ከኃላፊነታቸው በመነሳት በምትካቸው በተደረገው ሽግግር ዶክተር አብይ አህመድ ወደፊት መጡ። የዶክተር አብይ መንግስት በትረ-ስልጣኑን ከያዘ በኋላም ለኢትዮጵያ ፀሃይ ፈነጠቀች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሾሙ ሳምንት እንኳን ሳያስቆጥሩ ወደ ሱማሌ ክልል ጅግጅጋ በመጓዝና አብዛኛውን የአገሪቷን ክልሎችም በመዞር የጥፋት ጥላ አጥልቶባት የነበረችውንና አለመረጋጋትና ስጋት ያደረባትን አገር የማረጋጋትና ሰላም የማስፈን ስራን ከወኑ። ወደተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ከሕዝብ ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች፤ እንደ አገር ያስተላለፏቸው ውሳኔዎችና የሰጧቸው መንግሥታዊ መግለጫዎች ተስፋ ቆርጠው ለነበሩ የአገራችን ህዝቦች ዳግም ተስፋ ለመለመ፣ ተደፍተው የነበሩ አንገቶች ቀና አሉ፣ ተቆልፈው የነበሩ አንደበቶችም ተከፈቱ፤ አገራዊ ክንዋኔው እንደቀጠለ ለቀጠናዊና ለአህጉራዊ ብሎም ለአለም አቀፋዊ አገራት ግኙነትም ኢትዮጵያ የሚለውን ትልቅ ስም ተሸክመው ስራቸውን ማከናወን ጀመሩ። ኢትዮጵያና ኤርትራ አስታራቂ ሽማግሌ ተብሎ ለመጠቀሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀዳሚ በመሆን በበዓለ-ሲመታቸው ዕለት በፓርላማ ባሰሙት የሰላም ጥሪና ከዚያም በኋላ በሄዱበት ርቀት ሁለቱም አገሮች እርቅ አውርደዋል። ሁለቱ አገራት በስስት ዓይን የሚተያዩ አንድ አምሳል ሆነው በእኛነት መንፈስ በአንድነት ለመልማት፣ በአንድነት ለማደግ አንድ ቀበቶ ታጥቀው ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ነገር ሆኖ አለም እጁን በአፉ ጭኖ በአግራሞት ተመልክቷል። በየቀኑ አዳዲስና ያልተለመዱ ነገሮች በአገራችን መሆናቸው ቀጠለ፣ በዶክተር አብይ እና መንግስታቸው ፈጣን እንቅስቃሴም ብዙ የአለም አገራት ትኩረት ወደዚች ታሪካዊ አገር ኢትዮጵያ ሆነ። በየሄዱበት የጎረቤት አገራትም ከሚሰሩት የአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር ዜጎቼን ፍቱልኝ እያለ በሰው አገር ታስረው አስታዋሽ ያጡትን በርካታ ኢትዮጵያዊያን ራሳቸው በሚበሩነት አውሮፕላን ይዘው መምጣታቸውም ይታወሳል። ተስፋ ከሚያለመልሙ ተግባራት ባሻገር በአገሪቷ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋና ዴሞክራሲ እንዲያብብ በማሰብ ከአገር ውጪ ይንቀሳቀሱ የነበሩትን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደአገር ውስጥ መጥተው በተዘጋጀው መድረክ ለአገሩ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በሚል እሳቤ በሩን ክፍት አድርገውላቸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ንቅናቄዎች ወደ ኃላፊነት ከመጡባት ቀን ጀምሮ በነበሩት አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ “የመደመር” እሳቤያቸው በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የጋራ ዜማ መሆኑ እጅግ አስገራሚ ሆኗል። ኤርትራን ጨምሮ በበርካታ የጎረቤት አገሮች ባደረጓቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ያነሷቸው የሰላም፣ የፍቅርና የመደመር እሳቤ ውጤቶች ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካ፣ ከአፍሪካም ለዓለም ሕዝቦች የፍቅርና የመተሳሰብ አዲስ ብርሃን ፈንጥቋል። በኢትዮጵያ የመተሳሰብ ዘር ዘሪነት በአፍሪካ የሰላም ቀጣና በቅሎና አብቦ እንዲያፈራ የሚያስችል የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሰላምና የይቅር ባይነት ዝናብ በኢትዮጵያ ሰማይ ዘንቧል። ታዲያ ይህ በታሪኩ ሁሉ ለዓለም ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ታላቅ አርዓያ የሚሆን ሕዝብ በክብር በሚወዳት አገሩ ላይ መኖር ሲገባው አሁን አሁን ምንጫቸው ኢትዮጵያዊ ነው ለማለት የማያስደፍር፤ ወገን ከወገኑ ላይ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይታሰብና ፍጹም ሰብአዊነት የጎደላቸው ድርጊቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን እንገኛለን። ይህንን ኩሩ ሕዝብ ይዞ አገርን በዴሞክራሲና በብልፅግና ታላቅ ደረጃ ላይ ማድረስ ሲገባ፣ ነጋ ጠባ የሞት መርዶ መስማት እጅጉን ያሳምማል። አገር ሰላም ሰፍኖባት በብልፅግና ጎዳና መራመድ የምትችለው፣ ትውልድ በነፃነት እየኖረባት ሲቀጥል መሆኑ ፈጽሞ አያጠያይቅም። የትውልድ ቅብብሎሹ ውጤታማ ሆኖ ከከፍታው ማማ መድረስ የሚቻለው ደግሞ አገር በሕግ የበላይነት ሥር ስትመራ እንጂ ሁሉም እንዳሻው ጉልበተኛ ሲሆን፣ የአገር ሀብት ሲዘርፍ፣ የሰው ህይወት ሲጠፋና አገርን መከራ ውስጥ ሲጥል ዝም ማለት በትውልድም በታሪክም የሚያስጠይቅ ጉዳይ ነው። የተጀመረውን መልካም ጅማሮና የሰላም ጉዞ ያዩ፣ ከማህፀኗ ወጥተው ለዚች ብርቅዬ እናት አገራቸው የማይተኙ ለተራ ጥቅም የተገዙ የአስተሳሰብ ቆሻሻ የበዛባቸው ጥቂት ሸከም ዜጎቿ በዚህም በዚያም ክፍተት እየፈለጉ በብዙ ጥረትና ፈተና የመጣውን ብሩህ ጊዜ ለማጨለምና ጥላሸት ለመቀባት የሚሯሯጡ ብኩኖች አልጠፉም። በቅርቡ በሱማሌ ክልል እነዚሁ የእናት አገራቸው መልካም ጅማሮና የተስፋ ብርሃን መታየት ያላስደሰታቸው ሸክሞች የጥፋት ዱላቸውን በማንሳት ፤ በዘር በኃይማኖትና በተለያዩ ልዩነቶች ሰበብ ሽፋን በማድረግ በህዝቦች የማይተካ ውድ ህይወት ላይ፣ ዜጎች ጥረውና ለፍተው ለዘመናት ባፈሯቸው ንብረት ላይ ውድመትን በማስከተል አስለቅሰውናል አሳዝነውናልም፤ በሰላም ኑኗቸውን የሚኖሩትን ሰላማዊ ዜጎች ከቤታቸው ወጥተው እንዲሰደዱና መድረሻ እንዲያጡም አድርገዋል። አልፎ አልፎም በየቦታው ይህን ተግባራቸውን ለማይረባ የዝቅጠት ፖለቲካ ትርፋቸው የማይመለሰው የሰው ልጅ ወድ ህይወት ላይ አሹፈዋል። ይሄው ተግባራቸው የጣማቸው የወንድምን ደም ማፍሰስ ያስደሰታቸው የህሊና ባዶዎች ከሰሞኑ ደግሞ በቡራዩ፣ አሸዋ ሜዳ፣ ከታ እና ፊሊ ዶሮ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያና ጥቃቶች እንዲፈጸሙ፣ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ አድርገዋል። ይህ አይነቱን ተግባር በማን አለብኝነት የፈጸሙት ጨቃኞች ህግ የለም ወይ? የሚየስብል ጥያቄን እስከማስነሳት ደርሰዋል። በእርግጥ ህግ አለ አገሪቷ የምትተዳደርበት ለሁሉም ዜጎች እኩል የሚሰራ ህግ፤ እናም የመንግስት ትዕግስትና ከተግባራችሁ ተቆጠቡ ማሳሰቢያ ምንም ያልመሰላቸው እነዚህ የአገር ሸክሞች በማን አለበኝነት ለሰሩት ሥራ ዋጋ እንደሚከፍሉም ሕግ በተግባር እያሳያቸው ነው። ከዚህ ቀደም በሱማሌ ክልል የጥፋት ሰልፍ የተሰለፉም ሆነ ከዚያ በኋላ ለጠፉት ጥፋቶች እያንዳንዳቸው ዋጋ እየከፈሉ ነው። በቡራዩና አካባቢዋ ለተፈጠሩት ጥፋቶች አስካሁን ተጠርጥረው የተያዙ ከ400 በላይ አጥፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመልክቷል። በእርግጥ እንደ እኔ እምነት ለአንድ አገር እድገትና ብልጽግና ዴሞክራሲ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፣ ህዝቦች በነጻነት ሲንቀሳቀሱ መብትና ግዴታቸውን አውቀው ለአገር መልካም ቁመና ላይ ሲገኙ ዴሞክራሲ ያስፈልጋቸዋል ብቻ ሳይሆን ይገባቸዋል። አሁን ባለው የአገራችን ነባራዊ እውነታ ግን .. ገና መብትና ግዴታችንን ላላወቅነው ዴሞክራሲ ለህጻን ልጅ ውሃ በብርጭቆ እንደመስጠት ይሆንብኛል። በእርግጥ አንደ ታዋቂ የአገራችን ሰው ''ዴሞክራሲ ለአፍሪካ አይሆናትም ወይም ቅንጦት ነው'' ብሏል። አሁን የምናየውን የዴሞክራሲ አተገባበር ስቃኝ እውነቱን ነው ለማለት ይቃጣኛል። አንዱ አባራሪ ሌላው ተባራሪ ሆነን አገር ልታድግ አትችልም፣ አንዱ ጉልበተኛ ቀማኛ ሆኖ ሌላው ተበዳይ ሆኖ በዘር በፖለቲካ በኃይማኖት ተለያይተን አንድ አገርን በጋራ ማሳደግ ዘበት ነው። እኛ የሚያምርብን አንድነታችን ነው ፤ አንድነታችን ለውበታችን ብቻ አይደለም ሲጀመር እንደዚያ ካለሆንን በመለያየታችን ሽኩቻው ከበዛ ከራሳችን አልፈን ለውጪ ጠላት ራሳችንን አሳልፈን እንደምንሰጥ ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? ጥያቄው ለሁሉም ኢትዮጵያ ዜጋ ይሁንልኝ። ይህች ታሪካዊት አገርና ይህ ጨዋ ሕዝብ አሁን የሚታየው አሳዛኝና አሳፋሪ ነገር አይመጥናቸውም። ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ መሆኑ በእርግጠኝነት ሊታመንበት ይገባል።  በሰላም ወጥቶ መግባት የሚቻለው የሕግ የበላይነት ሲኖር፣ በእኩልነት የሚኖሩበት ስርዓት ሲፈጠርና ከብሔርተኝነት በላይ የጋራ አገር መኖር እሳቤን ማንገብ ሲቻልና ሲረጋገጥ ብቻ ነው። በአገራችን ዘላቂ ሰላምን፣ የልማት ተጠቃሚነትንና የሕዝቦች አንድነትን በማረጋገጥ ወደ ቀጣይ የልማትና የዕድገት ጉዞ ለመዝመት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የሪፎርም ስራዎች እየተሠሩ ነው። በአገር ውስጥ የሕዝብን አንድነት በማስጠበቅ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሰላም በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግሥት እያካሄደ ያለው አገራዊ ለውጥና ንቅናቄ በተለይም ለንግዱ ዘርፍ የላቀ ትርጉም አለው ብዬ አስባለው። እርግጥም ለአንድ አገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። እንደ ኢትዮጵያ ያለች ከድህነት ለመውጣት የምትታትር አገር ደግሞ ሰላምና መረጋጋቷን ማስጠበቅ ወሳኝ ተግባር መሆን ይገባታል። በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የሰላምና የመረጋጋት ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ሁሉም በኃላፊነት ስሜት ተባብረን መስራት አለብን። እርግጥ በየትኛውም አገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ኃይል አቅም ሊኖረው አይችልም፤ የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ፀረ-ሰላምነትን ማንገስ አይቻልምና ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ለማውደም አይበቃም። ዜጎች አገራችን ውስጥ ከተገኙት የልማት ውጤቶች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ይሁን እንጂ ተጠቃሚነታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንጂ ከሁከትና ከብጥብጥ አለመሆኑን ማወቅ ግድ ይለናል። የሰው ልጅ በህይወት መኖር ካልቻለ ስለሌላው መሰረታዊ መብቶች ማሰብ ከጉንጭ ማልፋት የዘለለ ሚና ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። እናም ሁሉም ዜጋ ስለ አገሩ ሰላም ይበልጥ ማሰብና መጨነቅ ይገባዋል። እርግጥ ለዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ለልማት መጠናከር ወሳኝ የሆነውን ሰላምን በጋራ ለማቆም መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰላማዊ የውይይት ባህልን እየገነቡ መሄድም  ልምድ ማድረግም ያስፈልጋል። ሰላምን ተጻርረው በአገራች ላይ ችግር ለመፍጠር የሚከጅሉ ሃይሎች ፍላጎታቸው የሰላም ሳይሆን የብጥብጥና የሁከት፣ የመብት ተጠቃሚነት ሳይሆን የመብት አዋኪነት ሁሉም በየደረጃው የሚጠቀምበት ሳይሆን የዜሮ ድምር ፖለቲካ ጫዋታን፣ የመከባበርና የመቻቻል ሳይሆን የጠባብነትና የትምክህተኝነት እንዲሁም የነጻነት መንገድ ሳይሆን የባርነት ቀንበር መሆኑ የማይታበይ ሃቅ ነው። የህዝብ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚያውኩና በሰላም ወጥቶ መግባት የሚሻን ህዝብ ከፍላጎቱ የሚያግድ ተግባራትን መታገል ያስፈልጋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። በሕግ የበላይነት ሥር የምትተዳደር ይቺ ሉዓላዊት አገር በህግ ያጠፋንም ለመቅጣት እንኳን በአይኗ ስር ተቀምጠው የሚቃዡትን ጥቂት የሰላም ጸሮችን ይቅርና በሰላምና ጸጥታ አስከባሪነት ከአገር አልፎ በአህጉራዊ ደረጃ የተመሰከረላት ብቁ የሰለጠነና ባለ አዕምሮ ዜጎች ያላት ናትና ከትዕግስት በላይ የሆነውን ተግባር በህግ ማስገዛት ትችላለች። ይህም ተግባር በቁርጠኝነት ተጀምሯል፣ የአገርን ሰላም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለማሸበር የሚያስቡትን የጥፋት እጆች ማሳጠር ቀላል ነውና ከማይረባው የእንቶ ፈንቶ እና የዜሮ ድምር የፖለቲካ ጨዋታ ወጥተው አገራቸውን በማሰብ ወደ አዕምሯቸው እንዲመለሱ ልብ ይስጣቸው እላለሁ። አገር እንደ አገር ቆማ እንድትሄድ የጸጥታ አካላት የሚያደርጉት ጥረትና ስራም ሙሉ እንዲሆን የእኛም አብሮነት ወሳኝ ነው። የምንገነባትን አዲሲቷን የተስፋ ምድር ኢትዮጵያ ስቃና ተደስታ ለማየት እጅ ለእጅ በመያያዝ ለጠላቶች አጥር መሆን አለብን። መንግስት በመንግስትነቱና በአስተዳዳሪነቱ የሚሰራቸውን ተግባራት ውሃ የሚደፉበትንና ጥላሸት የሚቀቡተን ኃይሎች በአይነቁራኛ በመጠባበቅ ሃሳቡን ማምከን የኛም ተግባር ነው። ለአገራችን፣ ለሰፈራችን ፣ፖሊስ ፣ የሰላም አስከባሪ፣ ህግ አስከባሪ፣ ጥፋተኛን ለህግ የማቅረብ ስራ የኔም ያንተም ተግባር ሊሆን ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰኔ 16ቱ የምስጋናና የድጋፍ ሰልፍ መድረክ ላይ ''ሁላችሁም በምትኖሩበት አካባቢና በምታደርጉት የየዕለት ኑሮ ለአገራችሁ ተቆርቋሪ ስትሆኑ በአቅማችሁ ለአገር ስትሰሩ ያኔ ምስጋናችሁ ሙሉ ይሆናል'' እንዳሉት ሁላችንም በምንኖርበት አካባቢ የዘር፣ የፖለቲካ፤ የኃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን ለአንድ አገራችን እንትጋ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትረጋገጠው በእኔ፣ በአንተ እና በሁላችንም ውስጥ ነውና ልዩነት በሌለበት ጦርነት ውስጥ ልዩነቶቻችንን ውበት አድርገን፣ አንድነታችንን አጠንክረን፣ የኖረ ታሪካችንን እያደስን ወደፊት እየሄድን ወደ ከፍታው ማማ ኢትዮጵያን ይዘን እንውጣ እላለሁ። መልካሙን ሁሉ ለኢትዮጵያ ተመኘሁ!                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም