የአዳማ ከተማና አካባቢዋ ወጣቶች ኦዴፓ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

68
አዳማ  መስከረም 13/2011 በሀገሪቷ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስ ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጎን በመሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን የአዳማ ከተማና አካባቢዋ ወጣቶች በድጋፍ ሰልፍ ገለጹ። የአዳማ ከተማና አካባቢዋ ወጣቶች የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በ9ኛው ጉባኤ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በመደገፍና ለተግባራዊነቱ ከፓርቲው ጎን በፅናት እንደሚቆሙ ለመግለጽ ዛሬ በአዳማ ከተማ ደማቅ የድጋፍ ሰልፍ አካሔደዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከተገኙት ወጣቶች መካከል ወጣት ሀብታሙ ብረሃኑ እንደገለጸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቷ ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲመጣ ወጣቶች በግንባር ቀደምትነት ታግለዋል። "ዛሬ የተገኘነውን ሃሳብን በነፃነት ማራመድ፣ ዴሞክራሲ፣ እኩልነትና ፍትህ በፅኑ መሰረት ላይ እንዲቆም፣ የተጀመረው ለውጥ እንዳይደናቀፍና ለውጤት እንዲበቃ መረባረብ አለብን" ነው ያለው። የድጋፍ ሰልፍ  የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ  ወቅቱ የሚጠይቀውን ትግል ለማካሄድና ለውጡን ወደ ፊት ለማራመድ በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ ከጎኑ ለመቆምና ለማጋዝ ያለንን አጋርነት ለመግለጽ ጭምር ነው ብሏል። በአሁኑ ወቅት ቄሮዎች፣ የተለያዩ የአገሪቱ ወጣቶችና መላው ህዝብ ባደረገው ትግል የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚደረገውን ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ከኦዴፓ ጎን በመቆም ለመመከት እንደሚሰሩም ተናግሯል ። "ሰሞኑን በቡራዩና አዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የታየው አፍራሽ ተግባር በጥፋት ቡድኖች የተሸረበ ሴራ እንጂ ለሰላም የታገለውን  ወጣት አይወክልም" ያለው ደግሞ ወጣት ባይሳ ወቅሹማ ነው። በቄሮዎችና በሀገሪቷ መላው ወጣቶች ግንባር ቀደም ትግልና መስዋዕትነት የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስ ለመከላከልና በኦዴፓ 9ኛው ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችን በመተግበር አገሪቱንና የኦሮሚያን ክልል ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል። "ወጣቶች ወሳኝ የለውጡ አካል እንደመሆናችን በትግላችን ያገኘነውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ በመላው ሀገሪቷ እንዲረጋገጥ የአፍራሽ ኃይሎች የጥፋት መሳሪያ ከመሆን ተቆጥበን የድርሻችንን እንወጣለን" ብሏል። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ድንቁ ቁንብ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት  ቄሬዎች ሽፋን በማድረግ እየተፈፀሙ ያሉት የጥፋት ተግባራት እንደማይወክሉን ሁሉም የክልሉ ወጣቶች ተገንዝበው ለለውጡ ውጤታማነት ከመንግስት ጎን በመሆን በአንድነት መስራት እንደሚገባ አመልክቷል። "ለውጡን ወደኋላ እንዲመለስ የሚጥሩ ኃይሎች በዋናነት መሳሪያ የሚያደርጉት ወጣቶችን ነው" ያለው ወጣት ድንቁ፣ ይህ ደግሞ የተጀመረው አገራዊ አንድነት ጎዞን የሚያደናቅፍና የሚያጨልም በመሆኑ ሁሉም ሊታገላቸው እንደሚገባ ገልጿል። መጨረሻውን በአዳማ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲዮም ባደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ መስፍን አሰፋ "ወጣቱ አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር፣ በመደማመጥና በመተባበር የተጀመረው አዲስ የለውጥ ጉዞ ለውጤት እንዲበቃ መረባረብ ይጠበቅበታል" ብለዋል። ኦዴፓ በጅማ ያካሄደው ዘጠነኛ ጉባኤ ፓርቲው አገሪቱ አሁን የደረሰችበትን ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው ማስቻሉን ተናግረዋል። አዲስ የትግል ስልት የተቀየሰበትና ውሳኔዎች የተላለፉበት ጉባኤ መሆኑንም ነው የጠቆሙት። ቄሬዎችና መላው የክልሉ ወጣቶች የተጀመረው ለውጥ እንዳይቀለበስና ለውጡን በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመገንባት በፓርቲው የተላለፉት ውሳኔዎችና የትግል ስልቶችን ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። "በሀገሪቷ ፍትህ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዘላቂ በሆነ ሁኔታ እውን እንዲሆን አብረን መስራት ይገባል" ብለዋል። በአዳማ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከአዳማ ከተማና አካባቢዋ የተወጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ቄሮዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆኖዋል ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም