ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል - ተፈታኝ ተማሪዎች

270

ወልዲያ/ሰመራ ጥቅምት 7/2015 (ኢዜአ) የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን በተረጋጋ መንገድ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል ሲሉ በወልድያና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች የሚፈተኑ ተማሪዎች ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በሁለተኛ ዙር የሚያስፈትኗቸውን ከ13 ሺህ 225 በላይ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከትላንት ጀምሮ እየተቀበሉ ነው።

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፈተናውን ለመውሰድ የተገኘው ተማሪ አበባው አማረ ፈተናው ከልጅነት እስከ ወጣትነት እድሜ የለፋንበት በመሆኑ በልዩ ትኩረት የምንወስደው ነው ሲል ለኢዜአ ተናግሯል።

"ፈተናውን በብቃትና በሰላማዊ መንገድ ተፈትኖ መጨረስ ከራሳችን አልፎ ለወላጆቻችን ልፋትና ድካም ዋጋ የምንሰጥበት በመሆኑ በተረጋጋ መንፈስ ለመውሰድ የስነ ልቦና ዝግጅት አድረጌያለሁ" ብሏል።

ፈተናው በዩኒቨርሲቲ መሰጠቱ የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ብቁ ዜጋ ለማፍራትና ከኩረጃ የጸዳ ትውልድ ለመቅረጽ የተወሰደ እርምጃ በመሆኑ መልካም አጋጣሚ አድርጎ እንደሚወስደው አመልክቷል።

''አዲስ የአፈታትን ስርዓት በእኔ ዘመን በመዘርጋቱ ደስተኛ ነኝ'' ሲልም አክሏል።

ተማሪ መልካም እሱባለው በበኩሏ "ከኩረጃ በጸዳና በራስ አእምሮ ፈተናን መፈተን የነገን ኃላፊት በብቃት ለመወጣት ያስችላል" ብላለች።

"የዘንድሮ የፈተና አሰጣጥ በእኛ ዘመን መጀመሩ እንደመልካም አጋጣሚ የምንወስደው ነው፤ ለነገው ትውልድም ጥሩ መሰረት የተጣለበት ነው" ስትል ገልጻለች።

"የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣቸውን ደንብና መመሪያዎች አክብሬ ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ ለመስራት ተዘጋጅቻለሁ" ብላለች።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ ግርማ በበኩላቸው በሁለተኛው ዙር የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ብሄራዊ ፈተና 10 ሺህ 25 ተማሪዎች ይፈተናሉ።

ተፈታኞቹ ፈተናውን በተሟላ መንገድ ማከናወን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

ከመጀመሪያው ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ተሞክሮ በመውሰድ ፈተናውን ተረጋግተው ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ለ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ናቸው።

ተማሪ ጻዲቅ አቦ እንዳለው  በቤተሰቦቹና በመምህሮቹ እገዛ ለፈተናው ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።

ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ በመውሰድ ስኬታማ ለመሆን በመጀመሪያው ዙር ፈተና ከወሰዱ ጓደኞቹ ተሞክሮ በመውሰድ የስነ-ልቦና ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።

ተማሪ አሚን አብዱሰላም በበኩሉ በዩንቨርስቲ ፈተናውን መፈተን መቻሉ ከኩረጃ በጸዳ መልኩ ፈተናውን ተረጋግቶ ለመውሰድ እድል የሚፈጥርለት በመሆኑ መደሰቱን ገልጿል።

የፈተናው አሰጣጥ በራስ የግል ጥረት የሚፈለገው ደረጃ ለመድረስ የሚያስችል መሆኑን ቀድሞ መገንዘቡን በመግለጽ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁሟል።

የ12ዓመት የትምህርት ጉዞ እኔና ቤተሰቦቼ የደከምንበት በመሆኑ ብሄራዊ ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ ሰርቼ በስኬት ማጠናቀቅ ቀድሞውንም ትልቁ እቅዴ ነው" ያለችው ደግሞ  ተማሪ ፈትህያ ደሊል ነች።

የሠመራ ዩንቨርስቲ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ግብረ-ሀይል  አስተባባሪ  ዶክተር  ጋሻው  ደሳለው ከጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ  በዩንቨርሲቲው  የሚጠሰውን  የተፈጥሮ  ሳይንስ ፈተና ለሚወስዱ ከ3ሺ 200 በላይ ተፈታኞች አቀባበል መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም