ኢትዮጵያ የሚገጥማትን ፈተና በመፍታት ረገድ ወጣቶች ከፍተኛ ሚና አለባቸው - በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬነር

70
አዲስ አበባ መስከረም 12/2011 ኢትዮጵያ በጀመረችው የልማት ጉዞ ውስጥ የሚገጥማትን ፈተና በመፍታት ረገድ ወጣቶች ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬነር ተናገሩ። 'ሶልቭ ኢት' በሚል መሪ ሀሳብ በአሜሪካ ኢምባሲ ድጋፍ ላለፉት አስራ አንድ ወራት ሲተገበር የቆየው የወጣቶች የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል። መርሃ ግብሩ በዋናነት ያልተማከለ የቴክኖሎጂ ፈጠራን እና ከባቢያዊ የፈጠራ ትስስሮችን መፍጠርን ዓላማው አድርጎ በዘጠኝ የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ሲተገበር ቆይቷል። የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድሩ የተካሄደባቸው አዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ሰመራ፣ ባህርዳር፣ ሃዋሳ፣ ጋምቤላ፣ ደሬዳዋ፣ እና ጅግጅጋ ናቸው። በነዚህ ዘጠኝ ከተሞች ተወዳድረው አሸናፊ የሆኑ 31 የፈጠራ ፕሮጀክቶች ለዛሬው የፍጻሜ ውድድር የቀረቡ ሲሆን፤ ውድድሩ ከጅማ በመጡ ሶስት ጓዶኛማቾች በቀረበው የህሙማን ኦክስጅን አቅርቦት መጣኝ ቴክኖሎጂ አሸናፊነት ተደምድሟል። በዝግጅቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬነር  "እናንተ የኢትዮጵያውያን ችግር በኢትዮጵያውያን መፈታት እንደሚቻል አስተምራችኋል" ሲሉ በውድድሩ የተሳተፉ ወጣቶችን አድንቀዋል። አምባሳደሩ አክለውም፤ የኢትዮጵያ የወደፊት ጉዞ እንቅፋቶችን በመፍታት ረገድ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት ወጣቶቹ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ በሚያከናውነው ተግባራት ውስጥ አገራቸው ከጎኑ እንደምትሰለፍ አረጋግጠዋል። በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ኢፍራ አሊ በበኩላቸው፤ መንግስት ወጣቶች ችግር ፈቺ በሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ እንዲሳተፉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት የፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች የሚያሰለጥንበት ትምህርት ቤት እያስገነባ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል። በውድደሩ የሁለተኛ ደረጃ፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን፤ በቅደም ተከተል ከአንድ እሰከ ሶስት ለወጡ የፈጠራ ፕሮጀክቶች  የሰባ አምስት፣ የሃምሳ እና የሃያ አምስት ሺ ብር ሽልማት ተበርክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም