በፌዴራሊዝም ሥርዓት አተገባበር የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የበይነ-መንግሥታት ግንኙነት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል

201

ጂማ፣ ጥቅምት 05 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት አተገባበር የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የበይነ-መንግሥታት ግንኙነት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ተነገሩ።

ጉዳዩን በበላይነት የሚመራው የፌዴሬሸን ምክር ቤት የበይነ-መንግሥታቱ አዋጅ ገቢራዊ እንዲደረግ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በጅማ ከተማ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ የሕግ አውጪዎች የምክክር መድረክ የበይነ-መንግሥታት ጉዳይ አንዱ አጀንዳ ተደርጎ ውይይት ተካሂዶበታል።

ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ከበጎ ጎኑ ባሻገር በአግባቡ ካልተስተናገደ የራሱ ስጋቶች እንዳሉት በምክክር መድረኩ በቀረበ ጽሑፍ ላይ ተነስቷል።

በአግባቡ ባልተስተናገደ ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት እያጋጠሙ ካሉ ፈተናዎች መካከል የመንግሥት መፍረስ፣ የፖለቲካ ዋልታ-ረገጥነት አስተሳሰብ ማደግ፣ በቁጥር አናሳ የሆኑ ሕዳጣን ቡድኖች መብት አለመከበር ተጠቅሰዋል።

በዚህም አገርን ከብተና ለመታደግ፣ ፖለቲካዊ ዋልታ-ረገጥነት ለማረምና የአናሳዎችን መብት ለማስጠበቅ የመንግሥታት ግንኙነት ወይም በይነ-መንግሥታት ጉዳይ ሁነኛ አማራጭ እንደሆነ የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓትን ከተከተለች 30 ዓመታት ቢቆጠርም የበይነ-መንግሥታት አዋጅ ግን ከ30 ዓመት በኋላ በ2013 እንደወጣ አንስተዋል።

ጠንካራ የመንግሥት ግንኙነት ካለ ችግሮች መፈታት እንደሚችሉ የተነሳ ሲሆን በክልልና በፌዴራል ብቻ ሳይሆን እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ግንኙነቱ መዳበር እንዳለበት አመላክተዋል።

የማስፈጸሚያ ደንቦች እየተዘጋጁ ስለመሆኑም ተገልጿል።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ የተጀመረውን የበይነ-መንግሥታት ግንኙነት ለማጠናከር ተቋማትና የሕግ ማዕቀፎችን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ  እንደሚገባ አመልክተዋል።

የበይነ-መንግሥታት ግንኙነት ተቋምና ሕግ ማዕቀፍ መዘርጋት ክልላዊና የዘርፍ ተቋማትን ማጠናከር፣ ተናቦ ለመሥራት እንደሚያግዝ እንዲሁም ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ሥራ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ይህን ለማድረግም ፍትሃዊነትና እኩልነትን ማስፈን እንዲሁም የጋራ እሴቶችን በትምህርት ሥርዓቱ፣ በኪነ- ጥበቡና በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች ማጠናከር እንደሚገባ አባላቱ አንስተዋል።

በመንግሥታት መካከል የሚኖረው የበይነ-መንግሥታት ግንኙነት ተጠያቂነት ለማምጣትና ጤነኛ ያልሆነ ፉክክር በትብብር እንዲተካ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

ፌዴሬሽን ምክር ቤት የጀመራቸውን ተግባራት በማጠናከር አዋጁን ወደ ተግባር መለወጥ ይገባል ብለዋል።

የፌዴሬሸን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው፤ ከለውጡ በፊት ባለው መንግሥታዊ ሥርዓት የበይነ-መንግሥታት ግንኙነት እንዲኖር አልተፈለገም ነበር ብለዋል።

በለውጡ ማግስት ግን አዋጁን ከማውጣት ጀምሮ የተሰራው ሥራ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ገልጸው፤ ምክር ቤቱ የበይነ-መንግሥታት ቋሚ ኮሚቴ ስለማቋቋሙ አንስተዋል።

በተግባር ደረጃም የክልል ለክልል ግንኙነት፣ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣ የሕግ አውጪዎች መድረክን በአብነት ጠቅሰው፤ ግንኙነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በቀጣይም ሥራውን በተሟላ መልኩ ለመተግባር የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችና ማስፈጸሚያ ደንቦችን በማውጣት በስፋት እንደሚሰራበት አረጋግጠዋል።

ለዚህ ግን ክልሎችን ጨምሮ የሁሉንም ምክር ቤቶች አባላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም