በአመራረትና አስተዳደር ጉድለት ከደለል ወርቅ ተገቢው ጥቅም እንዳልተገኘ ተገለጸ

71
ሽሬእንዳስላሴ መስከረም 12/2011 በአመራረትና በአስተዳደር ጉድለት ሀገሪቷ ከደለል ወርቅ ክምችት ልታገኝ የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች በመቀሌ ዩኒቨርስቲ  አንድ የዘርፉ ምሁር አስታወቁ። በማዕድን አጠቃቀምና አስተዳደር ዙርያ ያተኮረ የምክክር መድረክ በክልል ደረጃ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ተካሒዷል። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምድር ሳይንስ መምህር ዶክተር ካሳ አማረ ትላንት በተካሔደው መድረክ ላይ እንዳሉት በክልሉ ያለው የማዕድን ሀብት ክምችት የአጠቃቀም ግንዛቤ ችግር ያለበት ነው። “በትግራይ ክልል በ21 ወረዳዎች የደለል ወርቅ ክምችት ቢኖርም በአግባቡ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ገቢ እየተገኘ አይደለም”ብለዋል። “በየደረጃው የሚገኙ የመስተዳድር አካላት ለዘርፉ የሚሰጡት ትኩረት አናሳ በመሆኑ የማዕድን ሀብቱ  ለግል ተጠቃሚዎች ይውላል” ብለዋል፡፡ በተቀናጀ መልኩ ሊመራ ባለመቻሉም በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ  እድገት ላይ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እያበረከተ እንዳልሆነ ገልጸው ዘርፉ በእውቀትና በተቀናጀ መልኩ ከተመራ  ከግብርናው  በማይተናንስ መልኩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል። ዘርፉ ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ እድል የመፍጠር እድልም እንደሚኖረው ተናግረው እየተሰተዋለ ያለውን ችግር ለመፍታት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ  መሆኑን ጠቁመዋል። በወርቅ ማዕድን ያለውን ህገ-ወጥ ግብይት ስርአት ለማስያዝ  በቅንጅት እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ በክልሉ የማዕድንና ኤነርጂ ኤጄንሲ የማዕድን ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ መረሳ ናቸው። የወርቅ ማዕድኑን የሚያመርቱ ወገኖች ህጋዊ በሆነ መንገድ ወርቅ ብሄራዊ ባንክ ለማስገባት እንዲችሉ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም ተናግረዋል። በህገ ወጥ መንገድ ወርቅ የሚገዙና የሚያዟዙሩ ወገኖችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በየደረጃው ከሚገኙ የመስተዳድር አካላት ጋር በመሆን የተቀናጀ ስራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል። የዞኑ ጸጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ትኩዕ ገብረ መድህን በበኩላቸው ለምርቱ መቀነስ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር እስከ ወረዳ ድረስ ባለው የጸጥታ መዋቅር የተጠናከረ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል። ሃገር ከምርቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ህጋዊ አሰራሮችን በመከተል መስራት ስለሚገባም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። ባለፈው ዓመት በክልሉ ሊመረት ከታቀደው 22 ነጥብ አምስት ኩንታል ወርቅ ውስጥ በአመራረት ድክመት፣በህገ-ወጥ እንቅስቃሴና በሌሎችም ምክንያቶች የተሰበሰበው ከሁለት ኩንታል ብዙም እዳላለፈ ከክልሉ ማዕድንና ኤነርጂ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም