የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ ልዑክና የጂቡቲ ወጣቶች አረንጓዴ አሻራቸውን በጂቡቲ አኖሩ

107

ጥቅምት 05/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ የወጣቶች ልዑክ ከጂቡቲ ወጣቶች ጋር አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ያለመ የችግኝ ተከላ መርሐግብር በጂቡቲ አርታ ክልል አካሄደ።
በመርሃ ግብሩ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር፣ የጂቡቲ የግብርና ሚኒስትር አሕመድ መሐመድ አዋሌህ፣ የጂቡቲ ባህልና ወጣቶች ሚኒስትር ሂቦ ሙሚን አሶዌህ፣ በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እንዲሁም የኢትዮጵያና የጂቡቲ ወጣቶች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሁለት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በጂቡቲ ያካሄደች ሲሆን፣ ዛሬም በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ልዑኳ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት ማፅናትን ያለመ የችግኝ ተከላ ለሦስተኛ ጊዜ አካሂዳለች።

በመር ሐግብሩ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿና ከመላው አፍሪካ ጋር ያላትን ትብብር በአረንጓዴ ዲፕሎማሲውም ለመድገም እየተንቀሳቀሰች መሆኑ ተመልክቷል።

ለዚህም ወደ ጂቡቲ ያቀናው የወጣቶች ልዑክ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ያለመ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አካሂዷል።

በችግኝ ተከላው የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር ኢትዮጵያና ጂቡቲ ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነታቸውን በአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርም እንደሚደግሙት ተናግረዋል።

የጂቡቲ የግብርና ሚኒስትር አሕመድ መሐመድ አዋሌህ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በጂቡቲ ያካሄዱት የችግኝ ተከላ የኢትዮጵያና የጂቡቲን ጥብቅ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።

የተተከሉ ችግኞችም ኢትዮጵያ ለጂቡቲ የምትሰጠውን ከፍተኛ ስፍራ የሚያመላክት ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

በአረንጓዴ አሻራው የተሳተፉት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ወጣቶች እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት የወደፊት የጋራ እጣፈንታ በወጣቶች የተባበረ ክንድ ብሩህ ይሆናል።

አክለውም የኢትዮጵያንና የጂቡቲን ወንድማማችነት የሚያጠናክሩ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም