በደብረ ማርቆስና አሶሳ ችግረኛ ለሆኑ 1ሺህ 120 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

61
ደብረ ማርቆስ/አሶሳ መስከረም 12/2011 በደብረ ማርቆስ ከተማ  በንግድ ስራ የሚተዳደሩ ግለሰብ ችግረኛ ለሆኑ 1ሺህ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ። በአሶሳ ከተማም ለ120 ችግረኛ ተማሪዎች ተመሳሳይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የደብረ ማርቆስ ከተማ ትምህርት ቤቶች የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ መኩሪያው እንደገለፁት አቶ ወርቁ አይተነው የተባሉ ግለሰብ ያደረጉት ድጋፍ በመማሪያ ቁሳቁስ እጦትና መሰል ችግሮች ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ያግዛል ። ድጋፉ ተማሪዎቹን ለተሻለ ውጤት የሚያነሳሳና ለሌሎች ግለሰቦችም አርአያ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል ። ግለሰቡን በመወከል ድጋፉን ያበረከቱት አቶ ዘለቀ ድልነሳ በበኩላቸው ድጋፉ የተደረገው ችግረኛ ተማሪዎች ያለስጋት ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማገዝ እንደሆነ ገልጸዋል። "ግለሰቡ ለድጋፉ 200 ሺህ ብር ወጭ አድርገዋል" ያሉት ተወካዩ ለተማሪዎቹ በነብስ ወከፍ የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን መለገሳቸውን አመልክተዋል ። ድጋፋን የመቀጠል ዓላማ እንዳላቸውም አስታውቀዋል ። ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የተማሪ  ወላጅ ወይዘሮ ሰርካለም ሰንደቁ በተሰማሩበት የቀን ስራ የሚያገኙት ገቢ አነስተኛ በመሆኑ ለሶስት ልጆቻቸው የመማሪያ ቁሳቁስ ለማሟላት ሰግተው እንደነበር ተናግረዋል ። "ግለሰቡ ለሁሉም ልጆቼ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ በማሟላታቸው ከጭንቀቴ ገላግለወኛል" ያሉት ወይዘሮ ሰርካለም ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል ። የስድስተኛ ክፍል ተማሪ አዳነች ሽፈራው በበኩሏ የሚያሳድጓት አክስቷ ችግረኛ በመሆናቸው ባለፈው ዓመት የመማሪያ ቁሳቁስ አጥታ ትምህርቷን እንዳቋረጠች አስታውሳለች ። "የተደረገልኝ ድጋፍ ዘንድሮ ትምህርቴን እንድቀጥል ስለሚያስችለኝ ተደስቻለሁ "ብላለች፡፡ በተመሳሳይ በአሶሳ ከተማ የአንድነት የበጎ አድራጎት ማህበር አባላትና የአቡበክር መስጂድ ምእመናን ለ120 ችግረኛ ተማሪዎች ትላንት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፍ ያደረጉት ወላጆቻቸው አቅመ ደካማ ለሆኑና በሞት ላጡ ህጻናት ተማሪዎች ነው ። የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ሰይድ አሊ እንደገለፁት ማህበሩ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ለችግረኛ ተማሪዎችና አቅመ ደካማ አረጋውያን ድጋፍ እያደረገ ነው ። ማህበሩ በዕለቱ ተማሪዎች  የደብተር ፣እስክሪብቶና ቦርሳ ድጋፍ በተጨማሪ ለአረጋውያን ብርድ ልብስ መለገሱን አመልክተዋል። የአቡበክር መስጂድ ምእመናን አሰተባባሪ ሼህ እንድሪስ አህመድ በበኩላቸው ምእመናኑ በቤተሰብ አቅም ማነስ የተነሳ ህጻናት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ማህበረሰባዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በማሰብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ። ድጋፍ የተደረገላቸው ህፃናት ወላጆች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም