በኢሉባቦር ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ 78 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

97

መቱ ጥቅምት 4/2015 (ኢዜአ) በኢሉባቦር ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ 78 'ቡኡራ ቦሩ' የተሰኙ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የዞኑ የትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በኢሉባቦር ዞን በሀሉ ወረዳ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተነገባው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቋል።

በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተገነቡ ከሚገኙ 153 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች 78 ያህሉ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ መግባታቸውን የዞኑ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አብዲሳ ገልጸዋል።

የተቀሩት 73 ትምህርት ቤቶች በጎ አድራጊዎች ሲገኙ በቀጣይ ግንባታቸው እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በዞኑ የተጀመረው የምገባ መርሐ ግብር ደግሞ በ439 ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሚሰጥና ከ147 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

ለመርሐ ግብሩ ቀጣይነትም የሕብረተሰብ ተሳትፎን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ከ275 ሚሊዮን ብር በላይ የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል አቶ ጌታቸው።

የኢሊባቡር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው የትምህርት ቤቶቹ ወደ ስራ መግባት ከዚህ ቀደም ቅድመ መደበኛ ትምህርት ዘርፍ የነበረውን ሰፊ ክፍተት እንደሚቀርፍ ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቶቹ አገልግሎት መጀመር ለትምህርት ጥራት አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች ተደራሽ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

በተጨማሪም መርሐግብሩ ከትምህርት ገበታ የሚቀሩትንና የሚያቋርጡትን ተማሪዎች ምጣኔ የመቀነስ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ነው አቶ እንዳልካቸው የገለጹት።

በኢሉባቦር ዞን በሀሉ ወረዳ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተነገባው ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወጪ እንደተደረገበት በምረቃ ስነ ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ አንድ ሺህ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ስራ መጀመራቸውን ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በክልሉ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለ የምገባ መርሐግብር ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም