በደቡብ ክልል ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ ለማካካስ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ

45
ሀዋሳ መስከረም 12/2011 በደቡብ ክልል ተፈጥሮ ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በተስተጓጎለው የመኽር እርሻ ምክንያት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ ለማካካስ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው በየደረጃው ከሚገኙ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሴክተር አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በመስኖ ልማትና ግብይት የ2010 በጀት ዓመት አፈጻፀምና ቀጣይ እቅድ ዙሪያ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል። በውይይቱ ወቅት የቢሮው ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የፀጥታ ችግር በመኽር እርሻ እንቅሰቃሴ አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል። አርሶ አደሩ ለመኽር ማሳው አስፈላጊውን እንክብካቤ ካለማድረግ ጀምሮ የእርሻ ስራውን በአግባቡ ባለማካሄዱና ሳይታረሱ የቀሩ ማሳዎች በመኖራቸው በተወሰነ ደረጃ የምርት መቀነስ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ ችግር ባልተከሰተባቸውና ስንዴ በኩታ ገጠም አምራች በሆኑት ከምባታ ጠንባሮ፣ ሀዲያ፣ ስልጤና ጉራጌ ዞኖች ከአምና የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የጸጥታው ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች ግን የግብርና ሰራው በአምናው ፍጥነትና ጥራት ልክ መሄድ እንዳልተቻለ ነው አቶ ጥላሁን የተናገሩት፡፡ የጸጥታ ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች የምርት መቀነስን ለማካካስ የመስኖ ስራዎችና ሌሎች አማራጮች  ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ በተጓዳኝም መስኖን በመጠቀም በኩታ ገጠም ማሳዎች ላይ በገበያ ላይ የተሻለ ዋጋ የሚያስገኙ ምርቶችን የማምረትና በመኽር ወቅት ያልታረሱ ማሳዎችን የማልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ አመላክተዋል ። የሀዲያ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት አኑሎ በበኩላቸው በዞኑ በቀጣዮቹ ወራት የአረምና የስንዴ ዋግ በሽታን የመከላከል ሰራዎች የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ከጸጥታ ችግሩ ጋር በተያያዘ ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ ለማካካስ በዞኑ 54 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት መታቀዱን  ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ በቀጣይ በማሳ ላይ የበሽታና የተባይ ክስተት እንዳይኖር የሰብል ጥበቃና ቁጥጥር ስራ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የከምባታ ጠምባሮ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አስራት ማቴዮስ ናቸው፡፡ ከመስኖ ልማት በተጓዳኝ አሁን እየጣለ ያለውን ዝናብ ውሃ በመያዝና እርጥበት በማቆየት የእርሻ ሰራውን ለማሳከት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ። በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት መርሀ ግብር ሁለት አስተባባሪ አቶ ምራ መሐመድ እንዳሉት በክልሉ 11 ወረዳዎች በመርሀ ግብሩ በተገነቡ የመስኖ ተቋማት 1ሺህ 300 ሄክታር መሬት እየለማ ይገኛል። "ከዘርፉ የተሻለ ምርት ለማግኘት ስራዎችን በወቅቱ ልንሰራ ይገባል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም