የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኞች በትምህርትም ሆነ በስነ-ልቦና ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል

178

ጥቅምት 04 ቀን 2015 (ኢዜአ)የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኞች በትምህርትም ሆነ በስነ-ልቦና ዝግጁ ሊሆኑ  እንደሚገባ አንድ የስነ-ልቦና ባለሙያ መከሩ።

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከወትሮው በተለየ መልኩ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲዎች ገብተው እንዲፈተኑ እየተደረገ ይገኛል።

የሁለተኛ ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎችም  ከጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደሚፈተኑባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ ይሆናል።

በመሆኑም ተፈታኝ ተማሪዎች በጥናት ወቅት ካደረጉት ዝግጅት በተጨማሪ የስነ-ልቦና ዝግጁነትም ሊኖራቸው እንደሚገባ የስነ-ልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የስነ-ልቦና ባለሙያው መቅድም ቢቃሞ፤ ብሄራዊ ፈተናው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጠቱ አዲስ ተሞክሮ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች  ለስነ ልቦና መረበሽ ከመጋለጥ ይልቅ ኩረጃን በማስቀረት በእውቀታቸው የሚሰሩበትን እድል እንደሚፈጥር ሊረዱ ይገባል ።

ፈተናው በዩኒቨርሲቲ መሰጠቱ በራሱ የተፈታኞችን ስነ-ልቦና በመገንባት በኩል ጠቀሜታ እንዳለው የሚያብራሩት ባለሙያው፤ ተማሪዎች በተረጋጋና በጥሩ መንፈስ በመፈተን እድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።

የዘንድሮው የፈተና ሂደት ከረዥም እርቀት ምልልስ በመገላገል ከሃሳብና ከእንግልት ነፃ በመሆን ተማሪዎች የሚፈተኑበት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ተፈታኝ ተማሪዎች በጥናት ካደረጉት ዝግጅት ባለፈ በስነ-ልቦናም ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት።

የሚፈተኑ ተማሪዎች በቂ ዝግጅት እስካደረጉ ለወሬ እና አሉባልታ ቦታ ሳይሰጡ በተረጋጋና በሙሉ ልብ ሆነው ፈተናቸውን መሥራት አለባቸው ሲሉ መክረዋል።

የአካልና የአዕምሮ ዝግጅት አድርጎ መፈተን ደግሞ ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተማሪዎች በቂ እረፍትና እንቅልፍ አግኝተው ለፈተና ከገቡ በተረጋጋና በአስተውሎት የመሥራት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

የመፈተኛ ቁሶችን በሟሟላት ቀድሞ መገኘት ተረጋግቶ ለመፈተን የሚያግዝ መሆኑንም ባለሙያው አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች ለፈተና የተመደቡ መምህራንም ተማሪዎች በተረጋጋ መልኩ እንዲፈተኑ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም