የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ62 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

231

ጥቅምት 04/2015(ኢዜአ) የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ62 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ እና የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ድጋፉን ለመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጅ አስረክበዋል።

ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ 62 ሚሊዮን 827 ሺህ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ እና ከ670 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የምግብና ሌሎች ቁሳቁስ ድጋፎችን አድርገዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ በድጋፍ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ ለኢትዮጵያ ክብር አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን በግንባር ለሚፋለመው ጀግና ሰራዊት ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።

በዛሬው እለት በሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው፤ ከሰራዊቱ ጎን መሆናቸውን ለማሳየትም የደም ልገሳ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።  

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ የተደረገው ድጋፍ ለሰራዊቱ ያለንን ፍቅርና አብሮነት ለማሳየት ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ በበኩላቸው፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱንና ተጠሪ ተቋማቱን ድጋፍ አድንቀው ለተደረገው ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የተቋማቱ አመራርና ሰራተኞች ከገንዘብ ድጋፉ ባለፈ ደማችንን በመለገሳችን ተደስተናል ብለዋል።

 በቀጣይም ለሰራዊቱ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም