የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2022 የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ መሆኑ ተገለጸ

1204

ጥቅምት 4/2015/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2022 ከአፍሪካ ምርጥ 10 አየር መንገዶች መካከል አንደኛ ደረጃን በመያዝ ግንባር ቀደምነቱን ማስቀጠሉ ተገለጸ።

እንደ ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ ዘገባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምቹ፣ ተመራጭና አስተማማኝ የበረራ አገልግሎት በመስጠት ለተከታታይ ሁለት ዓመታት የ1ኛ ደረጃን በመያዝ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ መሆኑን አረጋግጧል።

ከ1ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ከያዙት የአፍሪካ አየር መንገዶች መካከል ሁለቱ የብሔራዊ አየር መንገድ እንዳልሆኑ በዘገባው ተመላክቷል።

የአየር ትራንስፖርት ምቹ፣ የተቀናጀ፣ ተመራጭና ፈጣን መጓጓዣ መሆኑ ዓለም አቀፋዊ መስተጋብር የተሳለጠ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

አየር መንገዶች የጉዞ አግልግሎታቸውን ምቹ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ደንበኞቻቸውን ዘና የሚያደርጉ ሥርዓቶችን በመፍጠር የንግድ ውድድርን ለማድረግ ሲተጉ ይስተዋላል።

በዚህም "ስካይትራክስ ወርልድ ኤርላይን አዋርድ" አየር መንገዶች የሰጡትን የአገልግሎት ጥራት በመገምገም በዓለም አቀፍ ደረጃ የእውቅና ሽልማት የተሰጣቸውን የምርጥ አየር መንገድ ዝርዝር ይፋ ያደርጋል።

የምርጥ አየር መንገድ ዝርዝሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የተባለውን ዓመታዊ የአየር መንገድ ተሳፋሪ የእርካታ የዳሰሳ ጥናት ውጤት መሰረት ያደረገ ነው።

እ.አ.አ. ከመስከረም 2021 እስከ ነሐሴ 2022 ድረስ በርካታ የዳሰሳ ጥናት ግብዓቶችን በመጠቀም የመጨረሻ ውጤት ይፋ ተድርጓል።

በጥናቱ መሰረት ለሀገራቸው አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ 10 ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገዶች ይፋ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምቹ፣ ተመራጭና አስተማማኝ የበረራ አገልግሎት በመስጠት ቁጥር አንድ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ተሰኝቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚሰጣቸው ምቹ የበረራ አገልግሎቶች አንፃር የአንደኛ ደረጃ የሚገባው መሆኑን ከታሪኩ በመነሳት መመስከር እንደሚቻል ‘ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ' በድረ-ገጹ ባሰፈረው ጽህፍ ነው ያስነበበው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሰጣቸው ምቹ፣ ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎቶች የተለያዩ ዓለም አቀፍ የእውቅና ሽልማቶች ተችረውታል።

ራም በመባል የሚጠራው የሞሮኮ "ሮያል-ኤየር-ማሮክ" ደግሞ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ፤የደቡብ አፍሪካው "ሳውዝ-አፍሪካን ኤር-ዌይ" ደግሞ 3ኛ ደረጃን የያዘ መሆኑ በዘገባው ተመላክቷል።

ኬኒያ-ኤርወይ፣ኤር-ሞሪሽየስ ፣ኢጂብት-ኤር፣ ሩዋንዳ-ኤር፣ የደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ መርከብ ድርጅት የሆነው "ሴፍ-ኤር" አየር መንገድ፣ፋስት-ጀት" በሚል የሚጠራው የዚንባቡዌ አየር መንገድ፣ የኤር-ሲሼልስ የተባሉ አየር መንገዶች እንደቅደም ተከተላቸው ከ4ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃን በመያዝ ከአፍሪካ ምርጥ 10 አየር መንገዶች ውስጥ ተካተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም