ተቋሙ 378 የህግ ታራሚዎችን በይቅርታ ለቀቀ

81
ሆሳእና መስከረም 12/2011 የሆሳዕና ማረሚያ ተቋም የሀዲያን የዘመን መለወጫ የሆነውን "ያሆዴ መስቀላ" በዓልን ምክንያት በማድረግ 378 የህግ ታራሚዎችን በይቅርታ መልቀቁን አስታወቀ። የማረሚያ ተቋሙ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ሞገስ ባፌ  ለኢዜአ እንደገለፁት በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አዲሱን ዓመት በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር" የሚለውን መርህ መሰረት በማድረግ ታራሚዎቹ ይቅርታ ተደርጎላቸዋል። "ታራሚዎቹ በቆይታቸው የባህሪ ለውጥ ያመጡና በስነ-ምግባራቸው የታነፁ  በመሆናቸው በክልሉ ይቅርታ ቦርድ ይሁንታ አግኝተዋል" ብለዋል፡፡ ታራሚዎቹ ስለ ወንጀል አስከፊነትና ጉዳት ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉን ያመለከቱት ኃላፊው በበዓሉ ወደ ህብረተሰቡ በመቀላቀል በአዲስ መንፈስ የበደሉትን በይቅርታ እንዲክሱና የተጀመረውን ለውጥ እንዲደግፉ በማሰብ ይቅርታ እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል። ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች መካከል አቶ አብርሃም ከቦሬ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በፈጸሙት ወንጀል መጸጸታቸውንና የበደሉትን ማህበረሰብ በይቅርታ እንደሚክሱ ተናግረዋል። በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። "ወጣት እንደመሆኔ ብዙ መስራትና መለወጥ በምችልበት ወቅት እዚህ መገኘት አልነበረብኝ" ያለው ደግሞ ወጣት ተመስገን አበበ ነው፡፡ በተደረገለት ይቅርታ መንግስትን በማመስገን ስለ ወንጀል አስከፊነት ለህብረተሰቡ በማስተማር ለውጡን ለማስቀጠል የበኩሉን እንደሚወጣ ወጣት ተመስገን ተናግሯል። በይቅርታ ከተለቁት 378 የህግ ታራሚዎች መካከል 11 ሴቶች እንደምገኙበት ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም