የአማራ ክልል የሁለተኛ ዙር የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች በቂ የስነልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጠየቀ

177

ባህር ዳር ጥቅምት 3/2015 (ኢዜአ) የአማራ ክልል የሁለተኛ ዙር የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች በቂ የስነልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙላው አበበ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በመጀመሪያው ዙር አንዳንድ ተማሪዎች በፈተና የተከለከሉ ሞባይል፣ ሰዓትና መሰል ቁሶችን ወደ ፈተና ጣቢያ ይዘው ለመግባት ሲሞክሩ በተደረገ ፍተሻ መያዛቸውን አስታውሰዋል።

በመጀመሪያ ዙር ፈተና ላይ የተስተዋሉ ግድፈቶችና ድርጊቶች በተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች መደገም ስለሌለበት የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክትል ቢሮ ሀላፊው አሳስበዋል።

"የፈተና ኩረጃ በራሳቸው ጥረት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚችሉ ጎበዝ ተማሪዎችን እየጎዳ ነው" ያሉት አቶ ሙላው፣ ማንኛውም ተማሪ በኩረጃ ፈተናን ለማለፍ አስቦ ወደ ፈተና ጣቢያ መምጣት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን ለፈተና ከመንቀሳቀሳቸው በፊት የመጡበትን ዓላማ በአግባቡ እንዲያውቁ ተገቢውን ምክር ሰጥተው መላክ ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

በአማራ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ፀሐፊ ዶክተር አስማረ ደጀን በበኩላቸው በመጀመሪያው ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ባሳዩት የስነ-ምግባር ጉድለት ከ12ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች ከፈተና ውጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

መሰል ችግር በሁለተኛው ዙር የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እንዳይደገም ወላጆች ልጆቻቸውን መክረው እንዲልኩ ጠይቀዋል።

በተወሰኑ ተፈታኞች ላይ የተስተዋለው መጨነቅና መረበሽ በ2ኛው ዙር ተፈታኞች ላይ እንዳይደገም የስነ ልቦና ዝግጅት አድርጎ መምጣት እንደሚገባም መከርዋል።

በሁለተኛ ዙር ተፈታኝ ተማሪዎች ሰላምና ደህንነታቸው ተጠብቆ ፈተናቸውን በሰላም እንዲወስዱ ፖሊስ አስፈላጊው የፀጥታ ጥበቃ እንደሚያደርግም ተገልጿል።  

በሁለተኛ ዙር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ ከ119 ሺህ በላይ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ይቀመጣሉ ተብሏል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም