በቀጣይ አስር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ፣ በደቡብና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የግብርና እንቅስቃሴዎች አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል- ኢንስቲትዩቱ

271

ጥቅምት 3/2015/ኢዜአ/  በቀጣይ አስር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ አዝማሚያ በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ፣ በደቡብና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የግብርና እንቅስቃሴዎች አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደጠቆመው ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ቀጣይ አስር ቀናት በሰሜንና የሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ደረቃማ፣ ጸሐያማና ነፋሻማ አየር ሁኔታ ይጠበቃል።

በምዕራብ ኢትዮጵያ ደግሞ ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ፣ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያም መጠነኛ ዝናብ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

በዚህም ጅማ፣ ኢሊባቦር፣ በወለጋ ዞኖች፣ ባሌ፣ ቤኔሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብና ምዕራብ ጎንደር፣ በጎጃምና አዊ ዞኖች፣ ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች፣ ጉራጌ፣ ጋሞ ጎፋና ወላይታ የተቀራረበ ዝናብ ያገኛሉ።

ሰሜን ቦረና፣ ጉጁ ዞኖች፣ አርሲ፣ ሐረርጌ ዞኖች፣ ሐረሪ ክልል፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶና አዲስ አበባ አነስተኛ ዝናብ እንደሚጠበቅም አሳውቋል።

በተመሳሳይ በደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ተፋሰሶች የተሻለ እርጥበት እንደሚያገኙና ሌሎቹ አካባቢዎች ደረቅ እና ከፊል ደረቃማ ሆነው እንደሚቆዩ አመላክቷል።

በቀጣይ አስር ቀናት ያለው የአየር ሁኔታ አዝማሚያም በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ፣ በደቡብና በደቡብ ምስራቅ ለሚከናወኑ የግብርና እንቅስቃሴዎች አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ሰብል ስብሰባ እየተከናወነ በመሆኑ እርጥበቱ የሚጠበቅባቸው አካባቢዎች ላይ አስፈላጊውንም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም