የፓርቲው ሊቀመንበርና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሰመራ ሲገቡ አቀባበል ተደረገላቸው

66
ሰመራ መስከረም 12/2011 የአፋር ህዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር  ዶክተር ኮንቴ ሙሳ እና  የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ ገአስ አህመድ ዛሬ ሰመራ ከተማ ሲገቡ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ በአቀባበል ስነ-ስርዓት ወቅት የፓርቲው  ሊቀመንበር በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ በመደገፍ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ባለፈው ወር ከውጭ ወደ ሀገር መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች በተዘዋወሩበት ወቅት በየደረጃው  የሚገኙ የክልሉ መንግስት አካላት በተለይም የአፋር ህዝብ አቀባበል እንዳደረገላቸው በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ " በሃገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እስካሁን ወደአፋር ክልል አልደረሰም " ያሉት ዶክተር ኮንቴ ፓርቲው  የአፋር ህዝብ የሀገራዊ ለውጡ አካል እንዲሆን በሰላማዊ መንገድ የሚደርገውን ትግል በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይም የአፋር ህዝብን መብትና ጥቅም ለማስከበር ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ  አቶ ገአስ አህመድ በበኩላቸው በሀገሪቱ ለውጥ ማምጣት የተቻለው  ወጣቶች ባደረጉት ትግልና በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአፋር ወጣቶች  የአመለካከት ልዩነቶች ሳይገድባቸው ለአንድነት በመቆም ከታገሉ በክልሉ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማስከበር ለውጡን ማስቀጠል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ በአቀባበሉ ስነ-ስርዓት ወቅት የሰመራ ከተማ ነዋሪዎችና የአካባቢው አመራር አካላት  መገኘታቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም