የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የጁቡቲ የመረጃ ተቋም በድንበር አካባቢ የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሚያከናውኗቸውን ስምሪቶች አጠናክረው ለመቀጠል ውይይት አደረጉ

201

ጥቅምት 01 ቀን 2015 (ኢዜአ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በጅቡቲ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ሐሰን ሰይድ የተመራ ከሀገሪቱ የጸጥታና ደኅንነት አካላት የተወጣጣ የልዑካን ቡድን በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጉብኝት አካሂዷል፡፡

የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላና ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ለልዑካን ቡድኑ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን፤ ከጉብኝት መርሐግበሩ ጎን ለጎን በጁቡቲ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ሐሰን ሰይድ የተመራው ከሀገሪቱ የጸጥታና የደኅንነት አካላት የተወጣጣ የልዑካን ቡድን እና የኢትዮጵያ አቻ ተቋማት የተካፈሉበት የሁለትዮሽ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ሁለቱ ሀገራትም በድንበር እንዲሁም በቀጣናው በሚስተዋሉ የጸጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሚያከናውኗቸውን ስምሪቶች አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከዲፕሎማሲዊ ግንኙነት ባሻገር በጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የተሳሰሩ ሀገራት እንደመሆናቸው የጋራ የጸጥታና የደኅንነት ሥጋት እንዳለባቸው በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡

በተለይ ሽብርተኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ ሕገወጥ የገንዘብ፣ የመሣሪያና የሰዎች ዝውውር የጋራ የጸጥታ ሥጋት በመሆናቸው፤ ችግሮችን ለማስቀረት የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢትዮጵያና የጅቡቲ የመረጃና የጸጥታ አካላት በሁለቱ ሀገራት የድንበር አካባቢዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን እና ሕገወጥ ታጣቂዎችን ለመከላከል በጋራ የሚሠሩትን ተግባር ለማጠናከር መስማማታቸውን ያመለከተው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ መረጃ፤ ውይይቱ በድንበርም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሁለቱን ሀገራት ዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጿል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ደኅንነትና እጣ ፈንታ እጅጉን የተሳሰረ በመሆኑ የጅቡቲ መጠቃት በኢትዮጵያ ላይ እንደደረሰ እንደሚቆጠር በኢትዮጵያም የሚፈጸም ጥቃት ጅቡቲን እንደሚመለከት በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡

በዚህ መነሻነትም ጅቡቲ ከየትኛውም አካል የሚፈጸምባትን ትንኮሳና የሚያጋጥማትን የደኅንነት ሥጋት ለመቀልበስ ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጎን እንደምትቆም ተጠቅሷል፡፡

በውይይቱ የሁለቱ ሀገራት የመረጃና የጸጥታ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች መካፈላቸውን መግለጫው ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም