ከ290 ሺህ በላይ ሐሰተኛ ዶላር ይዞ የተገኘ አንድ ካሜሩናዊ በቁጥጥር ስር ዋለ

153

ጥቅምት 1/2015 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከ290 ሺህ በላይ ሐሰተኛ የአሜሪካ ዶላር ይዞ የተገኘ አንድ የካሜሩን ዜግነት ያለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ አንድ የካሜሩን ዜግነት ያለው ግለሰብ በመዲናዋ ሐሰተኛ የአሜሪካን ዶላር ይዞ ሲንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል።

ግለሰቡ በመንገድ ላይ የተለያዩ ግለሰቦችን በመተዋወቅና ሀሰተኛ ምክንያቶችን በመፍጠር በተለያዩ የቢዝነስ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት በሚል የስልክ አድራሻ ይለዋወጣል።

የሚያጭበረብረውም ወላጅ አባቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ይሰሩ እንደነበር በመግለጽ የተለያዩ ማታለያዎችን በመጠቀም ነው።

አባቱ ለዕርዳታ የሚውል 5 ሚሊዮን ዶላር አሰባስበው ገንዘቡን ለተፈለገው አገልግሎት ሳያውሉ በሞት ተለይተዋል በማለት የማታለያ መንገዶችን ይጠቀማል።

ከዚሁ  ገንዘብ ውስጥም 2 ሚሊዮን ዶላሩን በዲፕሎማቶች አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ አስመጥቶ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ መሰማራት እንደሚፈልግም እንዲሁ።  

በመሆኑም በተጠርጣሪው አማካኝነት የኢንቨስትመንት ስራ ላይ አብሮ መሳተፍ በሚል 1 ሚሊዮን 480 ሺህ ብር እንዲያዋጣ ጥያቄ የቀረበለት አንድ ግለሰብ ካሜሩናዊውን በመጠራጠር ለፀጥታ አካላት ጥቆማ መስጠት ችሏል።

በተሰጠው ጥቆማ መሰረትም ፖሊስ ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪው መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ/ም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው አያት አደባባይ ጣዕም ዳቦ ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በወቅቱም በግለሰቡ ላይ በተደረገ ፍተሻ 297 ሺህ 700 ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር፣ 3 ሺህ 600 ሀሰተኛ ብር ጨምሮ ሀሰተኛ ገንዘብ ለማዘጋጀት የሚጠቀምበት ማሽንና ሌሎች ኬሚካሎች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

በመሆኑም ተጠርጣሪው ከነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።

ህብረተሰቡ መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል  ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የጠቆመው ፖሊስ  ነዋሪው  የተለያዩ ወንጀሎች ሲገጥሙት ጥቆማ የመስጠት ልምዱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም