ፓርኮችን ከአደጋ ለመከላከል ማህበረሰብን ማዕከል ያደረገ የጥበቃ መርሃ-ግብር ያስፈልጋል

52
ጂንካ  መስከረም 12/2011 በኢትዮጵያ ፓርኮች ህልውና ላይ የሚታዩ አደጋዎችን ለመከላከል የየአካባቢዎቹን ማህበረሰብ ማዕከል ያደረገ የጥበቃና ልማት መርሃ-ግብሮችን መተግበር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል። ህገ-ወጥ እርሻ መስፋፋት፣ የመሬት ወረራ፣ ሰፈራ፣ የማዕድን ቁፋሮ፣ ልቅ ግጦሽ እና ያልተመጣጠነ ልማት በኢትዮጵያ የሚገኙ ፓርኮች ህልውና ላይ የተጋረጡ አደጋዎች መሆናቸውን ባለስልጣኑ ገልጿል። በአገሪቱ የሚገኙ ፓርኮችን ከአደጋ ጠብቆ ማቆየት እንዲቻል የተለያዩ የልማት መርሃ ግብሮች እየተተገበሩ መሆኑም ተገልጿል። ሆኖም በፓርኮቹ አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ ለፓርኮች ጥበቃ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ በመሆኑና በጥበቃ ተግባሩ ቅንጅት አለመኖር የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም። በዚህም የተነሳ በአገሪቱ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ፓርኮች ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ባለስልጣኑ አመልክቷል። በመሆኑም በፓርኮቹ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመከላከል የማህበረሰቡን አመለካከት በመቀየር፤ ተጠቃሚነቱንም በአግባቡ በማረጋገጥ ላይ ያተኮሩ የጥበቃና ልማት ውጥኖችን አጠናክሮ መተግበር ወሳኝ ነው ተብሏል። የማጎ ፓርክ መገኛ በሆነው ደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ በፓርኮች ጥበቃ ዙሪያ ያለፈው ዓመት የባለስልጣኑ አፈጻጸምና ቀጣይ እቅድ ዙሪያ ባለድርሻ አካላት እየመከሩበት ባለው መድረክ ላይ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ ያሉትን የፓርኮችና የዱር እንስሳት መጠለያ ችግሮችን ለማቃለል ማህበረሰባዊ ንቅናቄን ማዕከል ያደረገ ሥራ ወሳኝ ነው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት የፓርኮቹን ህልውና ለመፍታት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫና ፓርኩን የመታደግ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ በውዲ በበኩላቸው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ መስህቦች ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለመቅረፍ አስተዳደራቸው እየሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ችግሮቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት እንዲቻል መንግስት፣ ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡም በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አስተላልፈዋል። በተለይም ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የሚሰራው ስራ ለአካባቢው ነዋሪ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል። ለመጪዎቹ ሶስት ቀናት በሚቆየው ውይይት ላይ በአገሪቱ ከሚገኙ 27 ፓርኮች የተወጣጡ   ከ150 በላይ አካላትተሳታፊ ሆነዋል። በኢትዮጵያ ነባር ብሔራዊ ፓርኮች ትልቅ ችግር ውስጥ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በየጊዜው እየተጠየቀ ይገኛል። በተጠናቀቀው 2010 ዓ.ም የነበሩ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ በፓርኮች ላይ ጉዳት ደርሷል። በአመቱ አዲስ የተከፈቱ 3 ፓርኮችን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ 27 ፓርኮች በቃጠሎ፣ በምንጣሮና 'የተለያዩ ማእድናትን እናወጣለን' በሚል በመቆፈር ፓርኮቹ ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው። በ2010 ዓም ብቻ አቢያታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ ማእድንና አሸዋ ለማውጣት፣ ባሌ ተራሮች ወረራ፣ ነጭ ሳር ምንጣሮ፣ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሰደድ እሳትና መሬት ወረራ መፈጸሙን ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ችግሮችን ለመፍታት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ለመመለስ እየሰራ ይገኛል። ፓርኮች ሰፊ የሆነ የስራ ዕድል በመፍጠርና ገቢ በማስገባት ረገድ የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ቢሆንም ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እየተገኘ እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም