በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የልዑካን ቡድን በአይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ግሩፕ ዓመታዊ ስብስባ ለመሳተፍ ዋሺንግተን ዲሲ ገባ

214

ጥቅምት 01 ቀን 2015 (ኢዜአ) በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የልዑካን ቡድን በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ ግሩፕ ዓመታዊ ስብስባ ለመሳተፍ ዋሺንግተን ዲሲ ገብቷል።

ዓመታዊ ስብስባው “በቀውሶች ወቅት አንድነት” በሚል መሪ ቃል ትናንት ተጀምሯል።

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ ልዑካን ቡድን ትናንት ዋሺንግተን ዲሲ ደርሷል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በልዑካን ቡድኑ ውስጥ ተካተዋል።

ልዑካን ቡድኑ በዓመታዊ ስብስባው ላይ የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገኖች ውይይት ላይ በሚኖረው ተሳትፎ ዙሪያ በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክክር ማድረጉን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።

በገንዘብ ሚኒስትሩ የተመራ ልዑካን ቡድን በዋሺንግተን ዲሲ በሚያዚያ ወር 2014 ዓ.ም በተካሄደው የዓለም ባንክ ግሩፕና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባ መሳተፉ የሚታወስ ነው።

ትናንት በተጀመረው ዓመታዊ ስብሰባ የዓለም ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂኦርጂዬቫ ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶች መፍትሔ ማበጀት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ንግግር አድርገዋል።

በዓመታዊ ስብስባው የዛሬ ውሎ አይኤምኤፍ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ደህንነት ሪፖርት እንዲሁም የዓለም ባንክ ግሩፕ የ2023 የዓለም ኢኮኖሚ ትንበያውን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የቡድን 20 አባል አገራት የፋይናንስና የግብርና ሚኒስትሮች እንዲሁም የማዕከላዊ ባንክ ገዢዎች ስብስባም ይካሄዳል።

በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ ግሩፕ ዓመታዊ ስብስባ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የምግብ ዋስትና፣ የምግብና ነዳጅ ዋጋ መናር፣ የትምህርት ኢንቨስትመንት፣ የሰው ሃብት ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።

ዓመታዊ ስብሰባው እስከ ጥቅምት 06 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም