በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የዝናብ ስርጭት መጠን ይቀንሳል

74
አዲስ አበባ መስከረም 12/2011  በሚቀጥሉት 10 ቀናት የዝናብ ስርጭት መጠን እየቀነሰ እንደሚመጣ  የብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው  በሚቀጥሉት አስር ቀናት በተለይ የአገሪቱ ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ ክፍሎች የዝናብ ስርጭትና መጠን እየቀነሰ ይሄዳል። በመሆኑም ውኃ አጠር የሆኑ አካባቢዎች የሚገኘውን የዝናብ ውኃ የመሰብሰብና የማከማችት ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በሌላ በኩልም እርጥበታማው የአየር ሁኔታ በምዕራባዊው አጋማሽ ቀጣይነት ሲኖረው፤ በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎችም ላይ እየተስፋፋ ይሄዳል፡፡ በነዚህ የአገሪቱ ክፍሎች ደጋማ አካባቢ ላይ የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይጠበቃል። በአካባቢው ለሚኖሩት አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ሣርና ለመጠጥ ውሀ አቅርቦት ጥሩ አስተዋጽዕ እንደሚኖረውም ይታመናል ሲል ኤጄንሲው በመግለጫው አስታውቋል። በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች እርጥበቱ ቀጣይነት የሚኖረው በመሆኑ ቀደም ብለው ለተዘሩና አልፎ አልፎ ፍሬ በመሙላት ላይ ለሚገኙ፣ ዘግይተው ለተዘሩና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎችም ሆነ ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። በነዚህ አካባበቢዎች በአፈር ውስጥ በተከማቸው እርጥበት በመታገዝ በደጋማው አካባቢ ለሚዘሩ የጥራጥሬ ሰብሎች አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተጠቅሷል። በአንፃሩም በአካባቢው ለሚገኙ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለግጦሽ ሣር ልምላሜ የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም